ኢትዮጵያ ሰው ሠራሽ አስተውሎት ዩኒቨርሲቲ ለማቋቋም የሰነቀችው ርዕይ ሀገራችንን የአፍሪካ የቴክኖሎጂና የፈጠራ ማዕከል የሚያደርግ ታሪካዊ እርምጃ መሆኑን የአፍሪካ ኅብረት የትምህርት ክፍል ኃላፊ ሶፊያ አሺፓላ ገለጹ።
ኢትዮጵያ ሁለንተናዊ ብልፅግናዋን ለማረጋገጥ ዲጂታል ቴክኖሎጂን የኢኮኖሚ ምሰሶና የልማት ማሳለጫ በማድረግ አመርቂ ውጤት እያስመዘገበች ይገኛል።
በተለይም የዲጂታል ኢትዮጵያ ስትራቴጂ እና የአምስት ሚሊየን ኢትዮ-ኮደርስ መርሐ ግብር የዜጎችን የዲጂታል፣ የሰው ሠራሽ አስተውሎትና የዳታ ሳይንስ ዕውቀትና ክህሎት በማበልጸግ ረገድ ሰፊ አቅም እየፈጠሩ ነው።
ከዚህም በላይ የመንግሥት አገልግሎቶችን ጥራትና ተደራሽነት ያረጋገጠው የዲጂታላይዜሽን መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት በቁልፍ የኢኮኖሚ መሣሪያነት እያገለገለ ስኬት አስገኝቷል።
የአፍሪካ ኅብረት የትምህርት ክፍል ኃላፊ ሶፊያ አሺላ እንደገለጹት፤ ኢትዮጵያ በዲጂታል ቴክኖሎጂ መስክ ወሳኝ መደላድል በመፍጠር አበረታች ውጤት እያመጣች ነው።
በተለይም የሰው ሠራሽ አስተውሎትን ልማት ለማፋጠን የመጀመሪያውን ዩኒቨርሲቲ ለማቋቋም የወሰደችው ተነሳሽነት ከፍተኛ አድናቆት የሚቸረው ነው።
ይህ በኢትዮጵያ የተጀመረው የዲጂታል ቴክኖሎጂ ልማት አብዮት በሌሎች የአፍሪካ ሀገራት ተመሳሳይ ኢንቨስትመንቶች እንዲስፋፉ በር የሚከፍት ከመሆኑም በላይ በአህጉሪቱ የለውጥ ጉዞ ላይ ትልቅ መነቃቃትን ይፈጥራል።
የሰው ሠራሽ አስተውሎት ዩኒቨርሲቲ የማቋቋም ርዕዩ የወደፊቱን ትምህርትና ምርምር በተሻለ ጥራት በመቅረጽ ሀገሪቱን ፈር ቀዳጅ ያደርጋታል ብለዋል።
ይህም የሰለጠነና ብቁ የሰው ኃይል በማፍራት፣ በአፍሪካ የፈጠራ፣ የምርምርና የሰው ኃይል ልማትን የሚያፋጥን ዓለም አቀፍ የልማት አብዮት መሆኑን አብራርተዋል።
በአጠቃላይ የኢትዮጵያ የትምህርት መሠረተ ልማትን የማስፋፋት ተግባር የትምህርት ጥራትና ተደራሽነትን በማረጋገጥ ለአፍሪካ ሀገራት ጭምር በአርዓያነት የሚወሰድ መሆኑን መግለጻቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
በአንደኛና ቅድመ-አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ግንባታ እንዲሁም በዲጂታል ቴክኖሎጂ የታየው ውጤታማነት ሕፃናትንና ታዳጊዎችን በተሻለ ዕውቀትና ክህሎት በማበልጸግ ሀገር ተረካቢ ዜጋን ለማፍራት ወሳኝ ሚና ይጫወታል።
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: