እጅግ ውብ እና ማራኪ የሆነ የጥበብ ልብስ (ሸማ) ሲሠራ አልፎ አልፎ ድንገት ተውበው የተደረደሩት የልብሱ ክሮች ክፉኛ ይተበተባሉ፤ ይቋጠራሉ። በዚህ ወሳኝ ቅጽበት፣ ትዕግስት የሌለው ሸማኔ ቋጠሮውን በኃይል ሊጎትተው ወይም በስለት ሊቆርጠው ይሞክራል፤ ውጤቱም የልብሱን ድርና ማግ አፈራርሶ ውበቱን ማጥፋት ይሆናል። ብልህ ሸማኔ ግን ይህን መንገድ በፍጹም አይከተልም። ይልቁንም ቁጭ ብሎ፣ ጊዜ ወስዶ፣ በሰከነ መንፈስ እና በትዕግስት የተተበተበውን ክር ጥንቃቄ በተሞላው ጥበብ አንድ በአንድ ይፈታል። ቋጠሮም ተላቅቆ ሸማው መልክ ይይዛል፡፡ የኢትዮጵያችን የፖለቲካና የማኅበራዊ ትስስር 'ሸማም' ዛሬ የሚገኘው ልክ በዚህኛው መስቀለኛ መንገድ ላይ ነው፡፡
ሀገራዊ ምክክርም ልክ እንደዚሁ የሸማኔ ጥበብ ነው። የተለያዩ አመለካከቶች፣ ፍላጎቶችና ታሪካዊ ዳራዎች ያሏቸውን ዜጎች በአንድነት አዋሕዶ ጠንካራና ማራኪ ሀገርን የመገንባት ጥልቅ ሂደት ነው።
ለዘመናት በሀገራችን የተተበተቡ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ቋጠሮዎችን ለመፍታት የተጠቀምነው መንገድ "በኃይል መጎተትና መቁረጥን" ነበር። ችግሮቻችንን በጠረጴዛ ዙሪያ ቁጭ ብለን፣ ተደማምጠንና ተከራክረን ከመፍታት ይልቅ፤ የጠብመንጃን ቋንቋ ስንመርጥ ቆይተናል። በዚህም የተነሳ የሀገራችን "ሸማ" ሲቀደድና ውበቱን ሲያጣ ኖሯል። አሁን ግን አዲስ የታሪክ ምዕራፍ ላይ እንገኛለን። የተቋጠረውን ሁሉ በሰከነ መንፈስ የምንፈታበት የሀገራዊ ምክክር መድረክ ተዘርግቷል።
👉የተሳኩ ዓለም አቀፍ ሀገራዊ ምክክሮች
ምክክር ለአንድ ሀገር ምን ያህል የሕይወትና የሞት ጉዳይ እንደሆነ ለመረዳት የሌሎች ሀገራትን የ"ሽመና" ታሪክ መመልከት ጠቃሚ ነው። ደቡብ አፍሪካ ከአፓርታይድ (የዘር አድልዎ) ሥርዓት ወደ ዴሞክራሲ ስትሸጋገር ያካሄደችው የኮዴሳ (CODESA) ምክክር በዓለም ታሪክ በግንባር ቀደምትነት ይጠቀሳል።
በዘረኝነትና በጥላቻ ለዘመናት የተከፋፈሉ፣ በደም የተቃቃሩ አካላት በአንድ ጠረጴዛ ዙሪያ መቀመጥ እጅግ ከባድ ፈተና ነበር። ነገር ግን በምክክሩ ሂደት፣ ኔልሰን ማንዴላ እና ፍሬደሪክ ዴክለርክ ሀገሪቱን ከእርስ በርስ ጦርነት መታደግ የቻሉት ታላቅ ትዕግስት በተሞላው መደማመጥ ነው።
ሌላው አስደናቂ ምሳሌ የቱኒዚያው "የብሔራዊ ምክክር ኳርቴት" (National Dialogue Quartet) ነው። በፈረንጆቹ 2013 ሀገሪቱ ከአረብ አብዮት በኋላ ወደ ለየለት የእርስ በርስ ጦርነት ልትገባ አፋፍ ላይ በነበረችበት ወቅት፣ የሠራተኛ ማኅበራት፣ የንግድ ተቋማት፣ የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾችና የሕግ ባለሙያዎች በአንድነት በመሆን ፖለቲከኞቹን ወደ ጠረጴዛ አምጥቷቸዋል።
ይህ የምክክር ሂደት ቱኒዚያን ከመፍረስ ታድጓል። ለዚህም ታሪካዊ ሥራቸው የኖቤል የሰላም ሽልማት ተበርክቶላቸዋል። ቱኒዚያውያን የተማሩት ነገር ቢኖር፣ ሀገርን ማዳን የሚቻለው በመሣሪያ ሳይሆን፣ ሁሉንም ባሳተፈ ጥልቅ ሀገራዊ ምክክር መሆኑን ነው።
👉ምሁራን ስለ ምክክር ምን ይላሉ?
ታዋቂው የሰላም ግንባታ ምሁር ጆን ፖል ሌደራክ እንደሚሉት፣ "እውነተኛ ሰላም የሚመጣው የቆሰሉ ማህኅረሰቦች ቁስላቸውን አውጥተው የሚነጋገሩበትና የሚደማመጡበት መድረክ ሲፈጠር ብቻ ነው።"
ታላቁ የደቡብ አፍሪካ የሰላም አባት ሊቀ ጳጳስ ዴዝሞንድ ቱቱ በበኩላቸው፣ "ልዩነቶቻችን ሊያራርቁን አልተፈጠሩም፤ ይልቁንም አንዱ ለሌላው ምን ያህል እንደሚያስፈልግ እንድንገነዘብ እንጂ" በማለት የምክክርን አስኳል ያስረዳሉ።
እነዚህ መሪዎችና ምሁራን የሚነግሩን አንድ ትልቅ እውነት አለ። ሀገራዊ ምክክር ማለት የሐሳብ ልዩነትን ማጥፋት ሳይሆን፣ ክሮቹን (ልዩነቶችን) ሳንቆርጥ በአንድ ላይ አዋሕደን ጠንካራ ማኅበረሰባዊ ስምምነት ላይ መድረስ ማለት ነው።
👉የእኛ ሽመና እና ጥበብ
ማንኛውንም አዲስ ክህሎት ከዳር ሆኖ በመመልከት ብቻ መልመድ አይቻልም፤ መዋኘት የሚቻለው ውሃ ውስጥ በመግባት እንደሆነው ሁሉ። ለእኛ ለኢትዮጵያውያን የጠረጴዛ ዙሪያ ምክክር አዲስ ባህል ነው። በዚህ ሂደት ውስጥ እንቅፋቶች ሊያጋጥሙ፣ አለመግባባቶች ሊፈጠሩ፣ አልፎ ተርፎም ቋጠሮዎቹ ሊጠብቁ ይችላሉ። ነገር ግን ዋናው ቁምነገር ጠረጴዛውን አለመተው ነው። እየተነጋገርን እንማራለን፤ እየተማርን እንነጋገራለን።
በዚህ ታላቅ ሀገራዊ ሂደት ውስጥ ከፍተኛው ፈተና የሚመጣው "ከዳር ተመልካቾች" ነው። የገዛ ሀገራቸውን "ሸማ" አብረው መሥራት ሲገባቸው፣ ከዳር ቆመው "እንዲህ መሆን ነበረበት፣ እንዲያ ቢደረግ ኖሮ" እያሉ የሚያብጠለጥሉ ወገኖች አይጠፉም። ነገር ግን ኃላፊነት የሚሰማው ዜጋ መረዳት ያለበት፣ ለሀገራችን ችግሮች መፍትሔ የሚገኘው በራሳችን ማኅበራዊና ታሪካዊ እውነታዎች ላይ ተመስርተን ራሳችን ስንመክርበት ብቻ መሆኑን ነው። የሌላ ሀገር መፍትሔ እንዳለ ተገልብጦ እኛ ጋር አይሠራም፤ የራሳችንን ጥበብ ራሳችን መሸመን አለብን።
የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር የራሳችንን ሀገር ዳግም የምንሸምንበት ታላቅ የትውልድ አደራ ነው። በምክክሩ ጠረጴዛ ዙሪያ የተሰበሰባችሁ ኢትዮጵያውያን ሆይ፤ ከእናንተ የምንጠብቀው ትዕግስትን፣ አርቆ አሳቢነትንና እውነተኛ መደማመጥን ነው። ድርና ማጉን አስተካክለን፣ የሁሉንም ኢትዮጵያዊ ቀለም አዋሕደን፣ ቋጠሮዎቻችንን በፍቅር ፈትተን፣ ጠንካራ፣ ዴሞክራሲያዊትና ሰላማዊት ኢትዮጵያን ለልጆቻችን እናውርስ።
ታሪክ ዛሬን ይመዘግባል፤ የነገዋ ኢትዮጵያም የምትገነባው ዛሬ በምንዘረጋው የምክክር መሠረት ላይ ነው፡፡
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: