የጤና ሚኒስቴር ተላላፊ እና ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎችን ለመቀነስ ያለመ እና በ8 ክልሎች ከ41 ሚሊዮን በላይ ዜጎችን ተጠቃሚ የሚያደርግ ሀገር አቀፍ የተቀናጀ የጤና ምርመራ ዘመቻ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በአርባ ምንጭ ዙሪያ ወረዳ ላንቴ ቀበሌ በይፋ አስጀምሯል።
በሀገር አቀፍ ደረጃ ለ5ኛ ዙር የተጀመረው ይህ ዘመቻ፣ የተቀናጀ የማኅበረሰብ ጤና ፕሮግራምን የማጠናከር ዓላማ እንዳለው ተገልጿል።
የተቀናጀ የጤና ምርመራ ዘመቻው ከ400 በላይ ወረዳዎችን የሚሸፍን ሲሆን፣ በማኅበረሰብ አቀፍ ደረጃ የትራኮማ እና የዝሆኔ በሽታዎች መከላከያ መድኃኒቶች ይሰራጫሉ።
በተጨማሪም የወባ በሽታ መከላከያ የአልጋ አጎበር ዕደላ፣ የዓይን ጤና፣ የማህጸን ጫፍ ካንሰር እና የቲቢ በሽታ ልየታና ሕክምና አገልግሎቶች ይሰጣሉ ተብሏል።
ጤና ሚኒስቴር ከካርተር ሰንተር ኢትዮጵያ እና ከኦርቢስ ኢንተርናሽናል ኢትዮጵያ ጋር በመተባበር ያዘጋጀው ይህ ዘመቻ፣ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ብቻ 25 ወረዳዎችን በማካተት ከ1 ሚሊዮን በላይ የኅብረተሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ እንደሚያደርግም በወቅቱ ተገልጿል።
በማስጀመሪያ መርሐ ግብሩ ላይ በኢትዮጵያ የዓለም ጤና ድርጅት እና የአጋር ድርጅቶች ተወካይ ዶክተር ሳራይ ማሉሞ፣ የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ከፍተኛ አማካሪ አቶ ሌሊሳ አማኑኤል እና የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጤና ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ መና መኩሪያ እንዲሁም የተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች ተገኝተዋል።
በትዕግስቱ ቡቼ
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: