Search

የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት፡- የሉዓላዊነት ዓለት የልማት መሀንዲስና የቀጣናው የሰላም አምባሳደር

ሰኞ ሐምሌ 13, 2018 83

"የኩሩ ህዝቦች መኖሪያ የኅብረ ብሔር ቡቃያ የሰላም ተምሳሌት ዓርማ የቀለሞች ኅብር ኢትዮጵያ!" ይህ የክብርና የሉዓላዊነት  መዝሙር ስንኝ ተራ የቃላት ድርደራ ሳይሆን የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት የታሪክ የፅናትና የማንነት መልክ ቁልጭ አድርጎ የሚያሳይ የሕሊና ብሩህ መስታወት ነው።

የሀገር መከላከያ ሠራዊት የሀገርን ዳር ድንበር ከመጠበቅና የውስጥ ሰላምን ከማስከበር ባለፈ በምስራቅ አፍሪካና በአጠቃላይ በአህጉሪቱ አስተማማኝ ሰላምና መረጋጋት እንዲሰፍን ግንባር ቀደም ሚና እየተጫወተ የሚገኝ የሰላም ግንባታ ዋነኛ ምሰሶ ነው።

ሠራዊቱ የሀገርን ዳር ድንበርና ሉዓላዊነት ለማስከበር በማንኛውም ጊዜና ሁኔታ ዝግጁ የሆነ የተደራጀ ኃይል ሲሆን ከታሪካዊ ጠላቶችና የሀገርን አንድነት ሊያናጉ ከሚፈልጉ የውስጥ  እና የውጭ ኃይሎች የሚሰነዘሩ ጥቃቶችን በመመከት የኢትዮጵያን ህልውና ያስከብራል።

ይህ የማይበገር ጥንካሬው የሚመነጨው በልቡ ውስጥ ከነደደው የማያልቅ የሀገር ፍቅር እሳትና በውስጡ ከሰረጸው ጠንካራ ወታደራዊ ዲሲፕሊን ሲሆን ሠራዊቱ የብሔር፣ የሃይማኖት እና የፖለቲካ ወገንተኝነት ሳይኖረው የሁሉንም ኢትዮጵያውያን እሴትና አንድነት የሚወክል እውነተኛ የሕዝብ ልጅ ነው።

ሀገርን በመጠበቅና ዳር ድንበርን በማስከበር ረገድ በዓለም መድረክ ላይ ተወዳዳሪ የሌለው የታሪክን ታላላቅ ፈተናዎች በትከሻው የተሸከመ የሰላም ጽኑ ዐለት በመሆኑ የጦር ሜዳ ውሎው ስልታዊና አስፈሪ የሰላም ጊዜው ደግሞ ለህዝብ አጋዥና መከታ ነው።

ከተለመደው ወታደራዊ ግዳጅ ባሻገር ይህ የጀግኖች ስብስብ ጠመንጃ ብቻ ሳይሆን አካፋና ዶማም መያዝ የሚችል የልማት ግንባር ቀደም ኃይል ነው።

በኢትዮጵያ የብልጽግና ጉዞ ውስጥ በታላላቅ የልማት ፕሮጀክቶች በአረንጓዴ ዐሻራ ችግኝ ተከላ በታላቁ ሕዳሴ ግድብና በህዝባዊ አገልግሎቶች ላይ ቀዳሚ በመሆን ድህነትን የሚዋጋ የላብ አርበኛ ነው።

በክረምትና በበጋ መስኖ ልማት በሰብል ስብሰባ እንዲሁም በተፈጥሮ እና ሰው ሰራሽ አደጋዎች ወቅት ከሕዝብ ጎን በመሰለፍ የሀገርን የምግብ ዋስትናና ልማት የሚያፋጥን የሕዝብ ደራሽ በመሆኑ ሰላምን በደሙ ልማትንና ብልጽግናን ደግሞ በላቡ እያረጋገጠ የኢትዮጵያን ትንሳኤ እውን እያደረገ ነዉ።

በጦር ግንባር ጀግና በልማት ግንባር ደግሞ መሀንዲስ ሆኖ ሀገርን ወደ ታላቅ ከፍታ ይመራታል።የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ዝና እና ገናናነት በሀገር ውስጥ ብቻ የተወሰነ አይደለም በአህጉሪቱና በዓለም አቀፍ ደረጃ በተሰማራባቸው የሰላም ማስከበር ተልዕኮዎች ሁሉ ሰብዓዊነትንና የሕግ የበላይነትን ያስቀደመ የሌሎችን ህዝቦች ነፃነትና ክብር እንደ ራሱ አድርጎ የጠበቀ ተወዳጅና የተከበረ ኃይል ነው።

ሠራዊታችን ግንባር ቀደም ተዋናይ ሲሆን ሌሎችን ማክበርና ለተቸገሩት መድረስ ከአባቶቻቸው የወረሱት የደም እሴት በመሆኑ በተሰማራበት አህጉርና ቀጣና ሁሉ በህዝቦች ልብ ውስጥ የማይጠፋ የፍቅርና የታማኝነት ዐሻራ ጥሏል በዚህም የተነሳ በአፍሪካ ምድር ህዝቦች ዘንድ ተወዳጅ ነው።

ጎረቤት ሀገራት ጠንካራና ሰላማዊ እንዲሆኑ ማድረግ የኢትዮጵያም ሰላም መሠረት መሆኑን በመረዳት ሠራዊቱ ለቀጣናዊ ትስስርና ደህንነት ዘብ ቆሟል።

የወቅቱን የቴክኖሎጂና የጂኦፖለቲካዊ ለውጦች ከግምት ውስጥ በማስገባት የመከላከያ ሠራዊቱ ራሱን በዕውቀት፣ በስልጠና እና በዘመናዊ ትጥቅ እያደራጀ ይገኛል።

የአየር ኃይል የባሕር ኃይል እና የሳይበር ደህንነት መዋቅሮችን በዘመናዊ መልኩ መገንባቱ የሀገርን የረጅም ጊዜ ጥቅም ከማስከበር ባለፈ ለቀጠናው ሰላም አስተማማኝ ጋሻ ሆኖ እንዲቀጥል ያደርገዋል።

ባጠቃላይ የኩሩ ህዝቦች መኖሪያ የሆነችውን ኢትዮጵያን እንደ አክሊል ደፍቶ ቀለማቷን ጠብቆ ታሪኳን አድሶ ፈተናዎችን በብቃት ተሻግሮና በዘመናዊ ቴክኖሎጂ አግዞ የሚጓዘው የመከላከያ ሠራዊታችን የኢትዮጵያ ሕያው ህልውና የነፃነቷ ዐለት የብዝሃነቷ ውበት እና የነገው ታላቅነቷ እውነተኛ ዋስትና ነው።

በመሆኑም ይህንን የሀገር ኩራት የሆነ ሠራዊት በሀሳብ በሞራልና በሁሉም መስክ መደገፍ እያንዳንዱ ዜጋ ታሪካዊ ኃላፊነት ነው ክብር ለጀግናው የሀገር መከላከያ ሠራዊታችን።

በብሌን ደምበሎ

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: