Search

የድብቅ ሀብቶቻችን ትንሳኤ፡ የነገው የኢኮኖሚ ተስፋችን

ሰኞ ሐምሌ 13, 2018 73

የወርቅን እውነተኛ እና አብረቅራቂ ውበት ለማየት አቧራውን ማራገፍ ብቻ በቂ እንደሆነ ሁሉ፣ የኢትዮጵያ ቱሪዝምም ለዘመናት ከተዳፈነበት አዙሪት ወጥቶ ዛሬ ላይ የሀገሪቱ የኢኮኖሚ ዋነኛ ምሰሶ ወደመሆን ታሪካዊ ሽግግር እያደረገ ይገኛል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በቅርቡ እንዳስገነዘቡት፣ ይህ አስደናቂ ለውጥ የተገኘው ለዓመታት የተረሱና በአቧራ ተሸፍነው የቆዩ ድብቅ ሀብቶቻችንን ወደ ብርሃን በማውጣት ጭምር ነው።

ከረጅም ጊዜ መገለል እና ከጠባብ እሳቤዎች ተላቆ፣ ቱሪዝም አሁን ላይ አዲስ ሀገራዊ ትኩረት አግኝቷል። ከዚህ ቀደም ታሪካዊ ቅርሶች እንደ ሸክም እና ነጠላ ትርክት ማራገቢያ ይወሰዱ የነበረ ቢሆንም፣ ዛሬ ላይ ግን ይህ የተዛባ ምልከታ ሙሉ ለሙሉ ተቀይሮ ቅርሶች የሀገር የጋራ ማንነት እና የኢኮኖሚ ጥንካሬ መሰረት መሆናቸው በተግባር እየታየ ይገኛል።

ለአብነት ያህል፣ የላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት ከላይ ወደ ታች ተፈልፍለው የተሰሩበት የህንጻ ጥበብ የመላው አፍሪካውያን እና የኢትዮጵያውያን የጋራ ኩራት ነው። ይህንን በዓለም ላይ ወደር ያልተገኘለት ድንቅ ስራ ለማድነቅ ሀይማኖትም ሆነ ብሄር ሳይገድበን የሰው ልጅ የጥበብ ጥግ መሆኑን በኩራት መመልከት እንችላለን።

በተመሳሳይ የተፈጥሮ ድንቅ የሆነው የሶፍ ዑመር ዋሻ ለስብሰባ፣ ለመመገቢያ እና ለመማሪያ በሚያገለግሉ የተፈጥሮ ክፍሎቹ የጥንት ስልጣኔን ቁልጭ አድርጎ የሚያሳይ አኩሪ ሀብት ነው። መንግስት እነዚህን እና መሰል ሀብቶች በሰፈር እና በመንደር ከፋፍሎ ከማየት ይልቅ የጋራ ብሔራዊ ሀብት መሆናቸውን አምኖ በማልማት ላይ የሚገኝ ሲሆን፣ የቀድሞ ቤተመንግስቶች ሳይቀር ከእዳነት ወደ ከፍተኛ የገቢ ምንጭነት ተቀይረው የሀብት ማመንጫ መሆናቸው የዚህ አዲስ የቱሪዝም ትኩረት ትልቁ ማሳያ ነው።

በመደመር እሳቤ መሪነት ቱሪዝም ከግብርና፣ ኢንዱስትሪ፣ ማዕድን እና ቴክኖሎጂ ጋር በመቀናጀት ከአምስቱ ቁልፍ የኢኮኖሚ ምሰሶዎች አንዱ መደረጉ ዘርፉ የተሰጠውን ከፍተኛ ሀገራዊ ትኩረት በግልጽ ያረጋግጣል።

ከዚህም ባለፈ ባለፉት ስምንት ዓመታት ውስጥ ብቻ የፀሐይ አውሮፕላንን ጨምሮ ከ35 በላይ በህገወጥ መንገድ የተዘረፉ የኢትዮጵያ ቅርሶች ወደ ሀገር እንዲመለሱ መደረጉ የባህል ሉዓላዊነታችን ማረጋገጫ ነው።

ቅርስን የማስመለስ፣ የመጠገን እና አዳዲስ የቱሪዝም መዳረሻዎችን የመገንባት ስራዎች ከቱሪዝም ልማት ጋር ተቀናጅተው በመሰራታቸው፣ ለሀገር የውጭ ምንዛሪ ገቢ ከማስገኘትና ገጽታን ከመገንባት ባሻገር የመደመርን እሳቤ በተግባር በማስረጽ ሀገራዊ አንድነትን ለማምጣት ከፍተኛ ሚና እየተጫወቱ ይገኛሉ።

ይህን ግዙፍ እና ያልተነካ ሀብት ሙሉ ለሙሉ ጥቅም ላይ ለማዋል የህዝብ፣ የግል ባለሀብቱ፣ የመንግስት እና የውጭ አጋሮች የተቀናጀ ኢንቨስትመንት እና ትብብር እጅግ ወሳኝ ነው።

ከኢንቨስትመንቱ እኩል ደግሞ ሀገርን የማስተዋወቅ ሰፊ ስራ መስራት የሚያስፈልግ ሲሆን፣ በተለይም ሀገርን በእግር በመዞር ድብቅ የቱሪዝም ሀብቶቻችንን አውጥቶ ለዓለም ማስተዋወቅ ይገባል። ሀገር ወዳድ እና አርቆ አሳቢ ወጣቶች ሲበዙ ቱሪዝም የማስተዋወቁ ስራ በከፍተኛ ፍጥነት እንደሚያድግ እና የዜጎች የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት በሰፊው እንደሚረጋገጥ ይታመናል።

የቱሪዝም አቧራውን ማራገፍ እና የተዳፈነውን ሀብት ማውጣት የነገዋ ኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ከፍታ ዋነኛ ማዕዘን ሆኖ በቀጣይነት ይቀጥላል።

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: