Search

ተመካካሪዎች በስምንቱ ዋና ዋና አጀንዳዎች ላይ ወደ ዝርዝር ምክክር ገቡ

ሰኞ ሐምሌ 13, 2018 84

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን አጠቃላይ የቅድመ ምክክር ውይይቶችና የሂደት ግንዛቤ ማስጨበጫ መድረኮችን አጠናቆ፣ ከ4,000 በላይ ተመካካሪዎችን በአዲስ አበባ ያካተተውን ትልቁን የውይይት ምዕራፍ በይፋ ማስጀመሩን የኢትዮጵያ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን ኮሚሽነር አምባሳደር ማህሙድ ድሪር አስታወቁ።

ኮሚሽኑ ይፋ ባደረጋቸው ስምንቱ ትልልቅ የምክክር አጀንዳዎች ላይ ተመድበው የነበሩት ተመካካሪዎች፣ ባለፉት ቀናት በአሰራር ስነ-ዘዴዎች ላይ ጥልቅ ግንዛቤ ከወሰዱ በኋላ ዛሬ ላይ ሆነው በሰከነ መንፈስ ወደ ውይይት ተሸጋግረዋል።

ሂደቱን ይበልጥ ውጤታማ ለማድረግም ተመካካሪዎቹ በስምንት ዋና ዋና አጀንዳዎች ስር ተከፋፍለው፣ በአጠቃላይ 80 አነስተኛ አጀንዳዎች ላይ በመወያየት ላይ ይገኛሉ።

በአንድ አጀንዳ ላይ 500 ተመካካሪዎችን የያዘ አብይ የስራ ቡድን መዋቀሩን ጠቅሰው፥ በእነዚህ አብይ ቡድኖች ስር እያንዳንዳቸው 50 ተመካካሪዎች ያሏቸው 10 ንዑስ ቡድኖች በማዋቀር ስራውን ጀምሯል።

ዛሬ የተጀመረው ይህ ቁልፍ የምክክር ምዕራፍ፤ ተመካካሪዎች ሃሳባቸውን በነፃነት የሚያንሸራሽሩበት፣ የሌሎችን አመለካከት በትዕግስት የሚሰሙበት እና የተለያየ ሃሳቦች በዴሞክራሲያዊ መንገድ የሚስተናገዱበት ታሪካዊ ምዕራፍ መሆኑ ታውቋል።

ይህንን ግዙፍ ሀገራዊ ሂደት በብቃት ለመምራትና ለማስተባበር ኮሚሽኑ በስራ ልምዳቸውና በትምህርት ዝግጅታቸው ታዋቂ የሆኑ 160 አመካካሪዎችን እንዲሁም 256 የቃለ ጉባኤ ጸሐፊዎችን በቦታው አሰማርቶ ስራውን በይፋ አስጀምሯል።

የኢትዮጵያን የነገ ዕጣ ፈንታ ለመወሰን የተሰበሰቡት እነዚህ 4,000 ኢትዮጵያውያን ዛሬ የጀመሩት ውይይት፣ የኢትዮጵያን  ሰላም እና አብሮነት በሚያረጋግጥ አግባብ በጥሩ ሁኔታ እየቀጠለ እንደሚገኝ የኮሚሽኑ ኮሚሽነር አምባሳደር ማህሙድ ድሪር ገልጸዋል።

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: