ሀገር ግንባታ በሕዝቦች መካከል በሚፈጠር የጋራ መግባባት፣ መደማመጥ እና በምክክር ላይ የሚመሠረት ዘላቂ የታሪክ ሒደት ነው።
ኢትዮጵያ ያሏትን የፖለቲካ፣ የታሪክ እና የማኅበራዊ ልዩነቶች በሠለጠነ መንገድ ለመፍታት እና የነገዋን ጠንካራ ሀገር ለመገንባት የመረጠችው ሁሉን አቀፍ የምክክር መንገድ፣ የብሔራዊ አንድነቷን መሠረት በጽኑ የሚያንጽ ታሪካዊ እርምጃ ነው።
በጠረጴዛ ዙሪያ ተቀምጦ የመደማመጥ እና የመመካከር ባህል ሲጎለብት ሀገርን ወደ ኋላ የሚያስቀሩ ጥርጣሬዎች እና አለመተማመኖች ተወግደው በምትካቸው የጋራ ራዕይ እና የታመነ የሀገር ሕልውና ይገነባል።
ምክክር ለሀገር ግንባታ በሚደረገው ጉዞ ውስጥ የሚኖረው ዋናው ፋይዳ በዋና ዋና የሀገር ሕልውና እና ብሔራዊ ጥቅሞች ላይ ወጥ የሆነ አቋም እንዲፈጠር ማድረጉ ነው።
በአንድ ሀገር ውስጥ የሚኖሩ የተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች፣ የፖለቲካ ኃይሎች እና የልሂቃን ስብስቦች በሀገራዊ ጉዳዮች ላይ በጋራ ሲመክሩ በውጭ ኃይሎች የሚሰነዘሩ የከፋፍለህ ግዛ ሴራዎችን ሙሉ በሙሉ የሚያከሽፍ የውስጥ ደኅንነት ይፈጠራል።
ኢትዮጵያ የጀመረችው ውይይት እና ምክክር ልዩነቶችን በመቻቻል ውስጥ በማድረግ ጥበብን የሚያሳድግ፣ የሕግ የበላይነትን የሚያስከብር እና የትውልድን ተስፋ የሚያለምልም ታላቅ የሀገር ግንባታ መሠረት ነው።
ምክክርን የሕልውናዋ አካል ያደረገችው ኢትዮጵያ የሁሉንም ዜጋ እኩል ተሳትፎ እና ባለቤትነት በማረጋገጥ ሒደቱን ጀምራለች።
ጅምሩ ለስኬት እንዲበቃ ደግሞ የሁሉም ኢትዮጵያዊ አስተዋፅኦ አስፈላጊ መሆኑ እሙን ነው።
በሐና ምንዳሁን
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: