የፖለቲካ ሥልጣንን በኃይል ለማቆየት ሀገርን በደም ሲያርስ የቆየው ሕገ ወጡ የህወሓት ቡድን፣ የራሱ የሆነ ፖለቲካዊ ቁመናም ሆነ ዓላማ የሌለው፣ የሌሎችን የጥፋት ሴራ ለመፈጸም ብቻ የተቀመጠ ደካማ ስብስብ መሆኑን በተግባር እያረጋገጠ ነው።
የትግራይም ሆነ የመላው ኢትዮጵያ ሕዝብ የሰጠውን ክብር እና ዕድል ሳይጠቀምበት ሀገር የማፍረስ አጀንዳን አንግቦ ወደ ጫካ የተመለሰው ይህ ቡድን፣ ዛሬ ላይ የራሱ ሕልውና የሌለው ተራ ተላላኪ እና የዘመን መጨረሻ ሽፍታ መሆኑን በግልጽ አሳይቷል።
ይህ የጥፋት ሎሌ አሁን ደግሞ የውድቀቱን የመጨረሻ እርከን በማሳየት ከፖለቲካ ድርጅትነት ወደ ሕገ ወጥ የሰው አዘዋዋሪነት ወርዷል።
የፌዴራል መንግሥት የሕዝቡን መከራ ለማቃለል የፕሪቶሪያውን ስምምነት ፈርሞ ሰላም ቢያመጣም፣ የጥፋት ጽንሱ የህወሓት ቡድን ግን ዛሬም የትግራይን ወጣቶች በግድ እያፈሰ በውክልና ጦርነት ለደካማው የሱዳን ጦር በቅጥረኛነት እየሸጣቸው መሆኑ የቡድኑን ተላላኪነት እና ርካሽነት በግልጽ የሚያሳይ ነው።
የዚህ ተላላኪ ቡድን መሪዎች የራሳቸውን ቤተሰቦች በአዲስ አበባ እና በውጭ ሀገራት በድሎት እያኖሩ፣ ምስኪኑን የትግራይ ወጣት ግን ለገንዘብ ማግኛ እና ለባዕዳን አጀንዳ ማስፈጸሚያነት በማያውቀው ጦርነት ውስጥ በእሳት እየማገዱት ነው።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) በቅርቡ ለፓርማ በሰጡት ማብራሪያ፣ ይህንን አሳዛኝ እውነታ ሲገልጹ፣ "ከሁሉ የከፋው አሁን በርካታ የትግራይ ልጆች በጉልበት ታፍሰው ሱዳን ላለው ጦርነት ተሽጠዋል። ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው አልበቃ ብሎ ጉዳዩ ወደ ሱዳን ተሸጋግሯል" በማለት የቡድኑን የማፊያነት ባሕሪ አጋልጠዋል።
ይህ አሳፋሪ ድርጊት የሚያረጋግጠው፣ ቡድኑ የራሱ ፖለቲካዊ ሕልውና የሌለው፣ ከፖለቲካ ድርጅትነት ይልቅ ዓለም አቀፍ የሰው አዘዋዋሪ እና የሌሎች ኃይሎች ጉዳይ አስፈጻሚ ሎሌ መሆኑን ነው።
በዚህ ሁሉ የጥፋት እና የውክልና ሴራ ውስጥ ትልቁን ዋጋ እየከፈለ ያለው የትግራይ ሕዝብ ነው።
መንግሥት የሰላም መንገዱን መርጦ የትግራይን ሕዝብ ከሞት አዙሪት ለማውጣት ቢጥርም፣ ይህ የራሱ ሐሳብና ራዕይ የሌለው የከሰረ ስብስብ ግን ሕዝቡን በባሰ አዘቅት ውስጥ ከትቶታል።
በአሁኑ ወቅት ከክልሉ ውጪ ያሉ ትግራዋይያን በሰላም ሲወጡ እና ሲገቡ፣ በክልሉ ውስጥ ያለው አፈሳ እና ጭቆና የሚያሳየው ሽፍታው ቡድን የትግራይን ሕዝብ እንደ ታጋች እየተጠቀመበት መሆኑን ነው።
በአጠቃላይ የፕሪቶሪያው ስምምነት የትግራይን ሕዝብ ከሞት ለማትረፍ የተዘረጋ የነፍስ አድን ገመድ ቢሆንም፣ በሰው ደም የሚነግደው ቡድኑ የገንዘብ ጥማት ይህንን ተስፋ እያጨለመው ይገኛል።
ሕልውናውን የሌሎችን የጥፋት አጀንዳ ከማስፈጸም እና ከሕዝብ እልቂት ጋር ያስተሳሰረው ይህ ተራ ተላላኪ ቡድን ከእንግዲህ ለትግራይ ሕዝብ የሚፈይደው ነገር የለም።
በመሆኑም የትግራይ ሕዝብ ይህንን ክብር የማይወድለት እና የባዕዳን አሽከር የሆነ የጥፋት ኃይልን "በቃህ!" እያለው ይገኛል።
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: