የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ዲኤታ አምባሳደር ሐደራ አበራ በዛሬው ዕለት በተካሄደው 1354ኛው የአፍሪካ ህብረት የሰላምና ደህንነት ምክር ቤት (AUPSC) በአፍሪካ ሽብርተኝነትን እና ጽንፈኝነትን መታገል በሚል ርዕስ በተዘጋጀው ሚኒስትሮች ስብሰባ ላይ ተሳታፊ ሆነዋል።
አምባሳደር ሐደራ በስብሰባው ላይ ባደረጉት ንግግር ዓለም አቀፍ የሽብር ቡድኖች በመላው አህጉሪቱ ሰላም እና ጸጥታ ላይ እየደቀኑት ያለው ስጋት እየጨመረ መምጣቱን አጽንኦት ሰጥተው ገልጸዋል።
የሽብር ቡድኖች አባላትን ለመመልመል፣ ፕሮፓጋንዳ ለማሰራጨት እና ጽንፈኝነትን ለማስፋፋት የዲጂታል መድረኮችንና ማህበራዊ ሚዲያዎችን ጨምሮ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን አላግባብ መጠቀማቸውን እንደቀጠሉበትም አምባሳደሩ ጠቁመዋል።
የአሁኑን ዓለም አቀፍ ሁኔታዎች ከግንዛቤ ውስጥ በማስገባት በአህጉሪቱ ውስጥ ያለውን የደህንነትና የመልካም አስተዳደር ትብብር ለማጠናከር የአፍሪካ ዝግጁ ኃይልን (Africa Standby Force) ወደ ስራ ማስገባት እና አህጉራዊ የህግ ማዕቀፎችን ትግበራ ማጠናከር አስፈላጊ መሆኑን አስገንዝበዋል።
በተጨማሪም አምባሳደር ሃደራ፣ ኢትዮጵያ የሀገር ውስጥ ሽብርተኝነትን ለመዋጋት የምታደርገውን ጽኑ ጥረት እና በክልሉ ያለውን የሽብር አደጋ ለመቅረፍ እያደረገች ያለችውን አስተዋጽኦ ማንሳታቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያመላክታል።
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: