የኮይሻ የኃይል ማመንጫ ቤት (Power House) የመጀመሪያ ምዕራፍ የስትራክቸራል ኮንክሪት ሙሌት ሥራ መጠናቀቁን የፕሮጀክቱ የሲቪል መሐንዲስ አስታውቀዋል።
መሐንዲሱ አቶ ይታገሱ አያሌው እንደተናገሩት ፕሮጀክቱ በኢትዮጵያ የኃይል ልማት ዘርፍ ከታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ እና ከጊቤ III የኃይል ማመንጫ ጣቢያዎች ቀጥሎ 3ኛ ደረጃ ላይ የሚገኝ ነው።
የግድቡ የአርማታ ሙሌት ግንባታ ከመከናወኑ በፊት ከ7 ሚሊዮን ሜትር ኪዩብ በላይ ልል አፈር የማንሳት ሥራ መሠራቱን ተናግረዋል።
በአሁኑ ወቅት ከ7 ነጥብ 725 ሚሊዮን ሜትር ኪዩብ የአርማታ ሙሌት ውስጥ ከ6 ነጥብ 2 ሚሊዮን ሜትር ኪዩብ በላይ የአርማታ ጥቅጥቅ ሙሌት መጠናቀቁንም ነው የጠቆሙት።
ግንባታውን ለማፋጠን በ2 ፈረቃ ለ24 ሰዓታት እየተሠራ መሆኑን የገለጹት አቶ ይታገሱ፣ በየወሩ በአማካይ ከ100 ሺሕ ሜትር ኪዩብ በላይ የአርማታ ጥቅጥቅ ሙሌት እየተከናወነ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
ግድቡ አሁን የደረሰበት ከባሕር ወለል በላይ ያለው ከፍታ 623 ሜትር ሲሆን፣ ይህም የግድቡ ቁመት አሁን ላይ 136 ሜትር እንዲሆን ማስቻሉን አንስተዋል።
እንደ አቶ ይታገሱ ገለጻ ግድቡ ሲጠናቀቅ ከባሕር ወለል በላይ ያለው ከፍታ 688 ሜትር ሲሆን፣ አጠቃላይ ቁመቱም 201 ሜትር ይደርሳል።
የመጀመሪያው ምዕራፍ የስትራክቸራል ኮንክሪት ሙሌት ሥራ መጠናቀቁን ተከትሎ የሁለተኛውን ምዕራፍ የኮንክሪት ሙሌት ለመጀመር የሚያስችሉ የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች በመከናወን ላይ እንደሚገኙም አስታውቀዋል።
ግድቡ እያንዳንዳቸው 300 ሜጋ ዋት የማመንጨት አቅም ያላቸው 6 ተርባይኖች ያሉት መሆኑን ጠቁመው፣ በአሁኑ ወቅት የኤሌክትሮ መካኒካል የተከላ ሥራ የሁሉም ተርባይኖች ክፍሎች በምርት ሒደት ላይ መሆናቸውን አብራርተዋል።
የግድቡ የውኃ ማስተንፈሻ በሮች ግንባታን ለማጠናቀቅ 7 ነጥብ 7 ሚሊዮን ሜትር ኪዩብ የልል አፈርና የጠንካራ ዓለት የቁፋሮ ሥራ የተከናወነ ሲሆን፣ የስትራክቸራል የአርማታ ሙሌት ሥራውም 45 በመቶ መጠናቀቁን ገልጸዋል።
የግድቡ ግንባታ እየተከናወነ የሚገኘው በምሥራቅ አፍሪካ ስምጥ ሸለቆ አካባቢ በመሆኑ፣ በቁፋሮ ወቅት የሚያጋጥሙ የተለያዩ የዓለት አካላት ግድቡን በሚገባ መሸከም እንዲችሉ በዘመናዊ ቴክኖሎጂ የታገዘ ሥራ መከናወኑን አንስተዋል።
በዚህም በፕሮጀክቱ ላይ እየተሳተፉ የሚገኙ የሀገር ውስጥ ባለሙያዎች የቴክኖሎጂና የዕውቀት ሽግግር ተጠቃሚ መሆን መቻላቸውን የገለጹት አቶ ይታገሱ፣ ይህም ወደፊት ሀገሪቱ በምታከናውናቸው መሰል ግዙፍ ፕሮጀክቶች ላይ የበኩላቸውን አስተዋጽኦ ለማበርከት እንደሚያስችላቸው አስታውቀዋል።
ግድቡ ሲጠናቀቅ የሚፈጥረው ሰው ሠራሽ ሐይቅ በአካባቢው ያለውን የቱሪዝም መስህብነት ከፍ እንደሚያደርገው መግለጻቸውን ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።
መንግሥት በ'ገበታ ለሀገር' መርሐ ግብር በኩል ዘርፉን ለማነቃቃት የሰጠውን ትኩረት በመደገፍ በፕሮጀክቱ አካባቢ የተለያዩ ሥራዎች እየተከናወኑ እንደሚገኝም ተናግረዋል።
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: