የግብርና ሚኒስትሩ አቶ አዲሱ አረጋ ከፍተኛ ጥራት እና ዋጋ ያለው ቡና ለማምረት በሳይንሳዊ አሠራር ላይ የተመሰረተ እንክብካቤ ማድረግ ወሳኝ መሆኑን ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ በ2018 በጀት ዓመት ከቡና ኤክስፖርት 3 ነጥብ 1 ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር ገቢ በማስገኘት አዲስ ታሪክ ማስመዝገቧን ያስታወሱት ሚኒስትሩ፤ ይህ ስኬት የተመዘገበው ከቡና ምርት እስከ ዝግጅት እንዲሁም ለዓለም አቀፍ ገበያ እስከማቅረብ ድረስ በተሠራው የተቀናጀ ሥራ እና የአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ-ግብር በፈጠረው ምቹ ሁኔታ መሆኑን አስታውቀዋል።
በ2019 በጀት ዓመት እንደ ሀገር 550 ሺህ ቶን ቡና ለውጭ ገበያ በመላክ 4 ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር ገቢ ለማግኘት መታቀዱን ሚኒስትሩ አመልክተዋል።
ለዚህ እቅድ መሳካት የቴክኖሎጂ አጠቃቀምና በቂ እንክብካቤ ወሳኝ መሆኑን ያነሱት አዲሱ፣ በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል በጉራፈርዳ እና በደቡብ ቤንች ወረዳዎች የሚገኘውን እና በሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ ስር የሚተዳደረውን የባበቃ ቡና ልማት ድርጅት በምሳሌነት ጠቅሰዋል።
ድርጅቱ ካለው 10 ሺህ ሄክታር መሬት ውስጥ 5 ሺህ 677 ነጥብ 64 ሄክታሩ በቡና የተሸፈነ ሲሆን፣ ልማቱም በበቂ እንክብካቤ እና በቴክኖሎጂ ተደግፎ በጥሩ ደረጃ ላይ እንደሚገኝ አብራርተዋል።
በተለይም የዝናብ እጥረት ችግርን ለመፍታት በ200 ሄክታር ማሳ ላይ የጠብታ መስኖ ቴክኖሎጂን በመጠቀም እያለሙ መሆኑን እና ይህም አሠራር ከአንድ ሄክታር ይገኝ የነበረውን አማካይ የ10 ኩንታል የቡና ምርታማነት በእጥፍ በማሳደግ እስከ 20 ኩንታል እንዲደርስ ማስቻሉን በማኅበራዊ ትስስር ገጽ ባጋሩት መልዕታቸው አስገንዝበዋል።
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: