Search

ከጣና በለስ ፕሮጀክት ውድመት ጀርባ ያለው የግብጽ ስውር እጅ

ማክሰኞ ሐምሌ 14, 2018 229

የጣና በለስ ሁለገብ ፕሮጀክት የኢትዮጵያን የውኃ ሀብት የመጠቀም ራዕይ በተጨባጭ ወደ መሬት ያወረደ ታላቅ ሀገራዊ የልማት ጅማሮ ነው።

1950ዎቹ መገባደጃ ላይ ሰፊ ጥናት ተደርጎበት ወደ ተግባር የገባው ይህ ፕሮጀክት፣ በጣሊያን መንግሥት 300 ሚሊዮን ዶላር ድጋፍ እውን መሆን ጀምሮ ነበር።

በወቅቱም የፓዌ ከተማን ከመገንባት ጀምሮ ዘመናዊ ሆስፒታል፣ አውሮፕላን ማረፊያ፣ የግብርና ማቀነባበሪያዎች እና 220 ሺሕ ሔክታር ላይ የሚያርፍ ግዙፍ የመስኖ ልማትን በማካተት እጅግ ተስፋ ሰጪ ደረጃ ላይ ደርሶ እንደነበር ታሪክ ያስታውሳል።

ሆኖም ይህ ብሩህ ተስፋ በማጠናቀቂያው ዋዜማ ላይ በድንገት ፈርሶ የኢትዮጵያን ተስፋ አምክኗል።

ለዚህ ታሪካዊ ክህደት እና ውድመት ደግሞ የውጭ ታሪካዊ ጠላቶች በተለይም የግብጽ ስውር ሴራ እና የሀገር ውስጡ የከሰረው የህወሓት ቡድን ተላላኪነት ዋነኛ ተዋናዮች ነበሩ።

የግብጽ "ረጅም እጅ" እና የከሰረው የህወሓት ቡድን ተላላኪነት

የጣና በለስ ፕሮጀክት መውደም ከሀገር ውስጥ የፖለቲካ ትርምስ ባሻገር ጥልቅ የሆነ የጂኦ ፖለቲካዊ ሴራ ያረፈበት ነው።

ፕሮጀክቱ ሀገራችን በዓባይ ውኃ ላይ ያላትን ተጠቃሚነት በተግባር ያሳየ እና የኃይል ፍላጎቷን የሚሸፍን ግዙፍ የኤሌክትሪክ ግድብ ግንባታን ያካተተ በመሆኑ የካይሮን ባለሥልጣናት እንቅልፍ ነስቶ ነበር።

ግብጽ ይህንን ፕሮጀክት ለማክሸፍ መጀመሪያ በገንዘብ ድጋፍ አድራጊዋ ጣሊያን ላይ "በብሔራዊ ደኅንነታችን ላይ የተቃጣ ጦርነት ነው" በማለት ከፍተኛ ዲፕሎማሲያዊ ጫና አሳደረች።

ይህ ሙከራዋ ሲከሽፍ ደግሞ የውስጥ ኃይሎችን፤ በተለይም ለሥልጣን ሲል ሀገር ከማፍረስ የማይመለሰውን የሕዝብ ጠላት የሆነውን የከሰረው የህወሓት ቡድንን እንደ ዋና አስፈጻሚ በመጠቀም ፕሮጀክቱ ሙሉ በሙሉ እንዲደናቀፍ አድርጋለች።

የቴክኖሎጂ እና የመሠረተ ልማት ዘረፋ

የህወሓት ቡድን ዕድሉን አግኝቶ ማዕከላዊ ሥልጣኑን መቆጣጠሩን ተከትሎ የወሰደው የመጀመሪያ እርምጃ ይህንን ግዙፍ ፕሮጀክት ማቆም ነበር።

የጥፋት ተልዕኮው በዋናነት ቴክኖሎጂን እና ማኅበራዊ መሠረተ ልማትን ያነጣጠረ ሲሆን፣ በመቶዎች የሚቆጠሩ ዘመናዊ የግብርና ማሽነሪዎች (ትራክተሮች፣ ዶዘሮች እና ኮምባይነሮች) ሆን ተብሎ ተዘርፈዋል።

በዚህም ብሩህ ተስፋ አይቶ የነበረው ሰፋሪ አርሶ አደር ከዘመናዊ እርሻ ወደ ኋላ ተመልሶ በበሬ እንዲያርስ ተገድዷል።

በወቅቱ በዘመናዊነቱ አቻ ያልነበረው የፓዌ ልዩ ሆስፒታል የሕክምና ቁሳቁሶች፣ በሀገራችን የመጀመሪያው የነበረው የፋይበር ግላስ ቧንቧ ፋብሪካ፣ የውኃ እና ኤሌክትሪክ ዝርጋታዎች፣ እንዲሁም የተጀመረው የግድብ ሥራ ሙሉ በሙሉ ፈርሰው የዘረፋ ሰለባ ሆነዋል።

የካርቱም ስምምነት፦ የባንዳነት ማረጋገጫ

ይህ በኢትዮጵያ ላይ የተሠራ ስውር ደባ ሕጋዊ ሽፋን ያገኘው 1984 . በወጣው የካርቱም መግለጫ ነው። በወቅቱ በከሰረው የህወሓት ቡድን እና በሱዳን መንግሥት መካከል የተፈረመው ይህ ስምምነት፤ ኢትዮጵያ በውኃዋ ላይ በምታደርገው ልማት "የቅድመ ምክክር" እንድታደርግ የሚያስገድድ አንቀጽን አቅፎ ነበር።

ድርጊቱ ሀገራችን በዓባይ ላይ የምታደርገውን እንቅስቃሴ ለዓመታት የገደበ፣ ለግብጽ እና ሱዳን ያልተገባ የልብ ድፍረት የሰጠ እንዲሁም የግብጽን ፍላጎት በይፋ ያስፈጸመ ታሪካዊ ስሕተት ነበር።

የውድመቱ ጠባሳ እና ትምህርት

የፕሮጀክቱ መፍረስ ኢትዮጵያ በምግብ ራስን የመቻል እና ግዙፍ የኤሌክትሪክ ኃይል የማመንጨት ዕድሏን ለሁለት ዐሥርተ ዓመታት ወደ ኋላ እንድትገፋ አድርጎታል። ሀገራችን በዓባይ ላይ ታላላቅ ግድቦችን ዳግም ለመጀመር እስከ 2003 . የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ መሠረት ድንጋይ መጣል ድረስ እንድትጠብቅም አስገድዷታል።

የጣና በለስ ፕሮጀክት የፈረሰው በሀብት እጥረት ሳይሆን በግብጽ የጂኦ ፖለቲካ ሴራ እና በከሰረው የህወሓት ቡድን ክህደት መሆኑ ለሀገራችን ትልቅ የፖለቲካ እና የኢኮኖሚ ትምህርት ነው።

ይህ ታሪክ ብሔራዊ ፕሮጀክቶቻችንን ሁልጊዜም ከውጭ ጠላት እና ከውስጥ ባንዳ ነቅተን መጠበቅ እንዳለብን ለትውልድ የሚያስተምር ሕያው ማሳያ ነው።

በለሚ ታደሰ

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: