• ታዋቂ የኢኮኖሚ ሊቃውንት እንደሚያስረዱት፣ ወደብ አልባ ሀገራት ከአራቱ የልማት ማነቆዎች በአንዱ የተጠፈሩ ሲሆን፣ ገበያቸውም ጎረቤት ሀገር ብቻ በመሆኑ "የጎረቤቶቻቸው እስረኞች" ተብለው ይገለጻሉ።
• የወደብ አልባነት የአንድን ሀገር የወጪ ንግድ ከ33 እስከ 43 በመቶ ይቀንሳል።
• ኢትዮጵያ ከ130 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ ያላት በዓለም ትልቋ ወደብ አልባ ሀገር ስትሆን፣ ከባሕር ዳርቻ ያላት ርቀት ግን ከ60 ኪሎ ሜትር ያነሰ ነው።
• ኢትዮጵያ በታሪኳ ከጥንት ጀምሮ የራሷ የባሕር በር የነበራት ሀገር ነበረች። በአክሱም ዘመን ኢትዮጵያ በአዱሊስ ወደብ በመጠቀም ከግሪክ እና ባዛንታይን ጋር በሰፊው ትገበያይ ነበር።
• ፕሊኒ እና ኮስማስ የመሣሠሉ ጥንታዊ ጸሐፊዎች እንዳሰፈሩት፣ የአክሱም ነገሥታት በቀይ ባሕር ግዙፍ የባሕር ኃይል ነበራቸው። ንጉሥ አፄ ካሌብ ቀይ ባሕርን ተሻግረው የመንንና ደቡብ አረቢያን ይቆጣጠሩ እንደነበርም ታሪክ ይመሰክራል።
• አዱሊስ አገልግሎት ሲያቆም ኢትዮጵያውያን ምጽዋን፣ ቆይቶም በአርጎባ እና አፋር ነጋዴዎች አማካኝነት ዘይላን እና በርበራን ዋና ወደባቸው አድርገው ተጠቅመዋል።
• ከጥንት ጀምሮ እስከ ቅርብ ዘመናት ድረስ የቀይ ባሕር ጠረፍና አካባቢው (መረብ ምላሽ) "ባሕረ ነጋሽ" (የባሕር ንጉሥ/ገዢ) በሚባሉ በኢትዮጵያ ማዕከላዊ መንግሥት በሚሾሙ አስተዳዳሪዎች ሲመራ የቆየ ሲሆን፣ ይህም ኢትዮጵያ በባሕር በሯ ላይ የነበራትን ሉዓላዊ ባለቤትነት እና አስተዳደራዊ ቁጥጥር የሚያረጋግጥ ጠንካራ ታሪካዊ ማስረጃ ነው።
• ዳግማዊ አፄ ምኒሊክ ጅቡቲን እና የጋምቤላን ወደብ ለሀገር ጥቅም አውለዋል። እኚሁ ንጉሥ በ1868 ዓ.ም ለንጉሥ ኡምቤርቶ በላኩት ደብዳቤ "የዘይላ በር እጃችን ተመልሶ ገባ እንዲሉ" በማለት የወደብ ባለቤትነትን ለማረጋገጥ የነበራቸውን ጽኑ ፍላጎት ገልጸዋል።
• የኢትዮጵያ ነገሥታት ከ1885 ዓ.ም ጀምሮ የባሕር ጠረፎቻቸው በውጭ ኃይሎች ከተያዙባቸው ጊዜ አንስቶ፣ የባሕር በርን ማስመለስ የውጭ ግንኙነት ፖሊሲያቸው ዋነኛ አካል አድርገውት ነበር።
• ታላቁ የጦር መሪ ራስ አሉላ አባነጋ "ቀይ ባሕር የኢትዮጵያ የተፈጥሮ ወሰን ሆኖ ኖሯል፤ ይኖራልም!" በማለት የተናገሩት ታሪካዊ አባባል፣ ኢትዮጵያ ከባሕር በሯ ጋር ያላትን የማይፋቅ ታሪካዊና ተፈጥሯዊ መብት በሚገባ የሚያስረግጥ እና ትውልድ ሊዘነጋው የማይገባ የኅልውና ማረጋገጫ ነው።
• አሰብ የኢትዮጵያዊው አፋር ሕዝቦች መኖሪያ ነው። ጣሊያናዊው ጁሴፔ ሳፔቶ በ1822 ዓ.ም አሰብን ከሱልጣን ኢብራሂም በ6000 ማሪያቴሬዛ የገዛው አፄ ምኒሊክ ሳያውቁ ነበር።
• ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ፣ ኢትዮጵያ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እና አሸናፊ ከነበሩት ኃያላን መንግሥታት ጋር ባደረገችው ከፍተኛ የዲፕሎማሲ ትግል ታሪካዊ የባሕር በር መብቷን በማስከበር ዳግም ከባሕር ጋር መገናኘት ችላ ነበር።
• በፌዴሬሽኑ ዘመን እና ከዚያም በኋላ ኢትዮጵያ የሦስት ወደቦች ባለቤት እና አስተዳዳሪ በመሆን ሉዓላዊ አቅሟን አሳይታለች። በተለይም የአሰብን ወደብ ግዙፍ ግንባታ በማካሄድ ዘመናዊ የወደብ አገልግሎት እንዲሰጥ አድርጋለች።
• በዚህም መሰረት በተለይ በደርግ ዘመን አሰብ ዘመናዊ አውሮፕላን ማረፊያ፣ መንገዶች እና የነዳጅ ማጣሪያ ተሰርቶላት ዋና ወደብ ሆና ነበር። አሰብ በርካታ ኢትዮጵያውያን ሞቅ አድርገው የሚኖሩባት ከተማ ነበረች።
• ኤርትራ ከመገንጠሏ በፊት በነበረው የደርግ መንግሥት ዘመንም፣ ኢትዮጵያ አሰብን የራሷ "ራስ ገዝ አስተዳደር" በማድረግ በአዋጅ ጭምር አጽድቃ ታስተዳድር ነበር።
• በ1956 ዓ.ም (እ.ኤ.አ 1964) የአፍሪካ መሪዎች በካይሮ ባወጡት ህግ፣ አፍሪካውያን ሀገራት ነፃ ሲወጡ የነበራቸውን ግዛት ይዘው እንዲወጡ ወስነዋል።
• በዚህም መሠረት ኤርትራ ነፃ ስትወጣ አሰብ ራስ ገዝ አስተዳደር እንጂ የኤርትራ አካል አልነበረችም። ከሕዝብ ስብጥሯም 90 በመቶው አፋር ኢትዮጵያ ውስጥ ነው የሚኖረው።
• ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ ፖላንድ ከጀርመን የወደብ መተላለፊያ (ኮሪዶር) አግኝታለች። እንዲሁም በአፍሪካ ኮንጎ ብራዛቪል ከኮንጎ ኪንሻሳ መሬት ተሰጥቷት ወደ ባሕር እንድትዘልቅ ተደርጓል።
• ልክ እንደነዚህ ሀገራት ሁሉ፣ ኢትዮጵያም በድርድር የባሕር በር የማግኘት ህጋዊ መብት ነበራት።
• ነገር ግን በ1983 ዓ.ም ኤርትራ በሪፈረንደም ከኢትዮጵያ ስትገነጠል፣ በወቅቱ ስልጣን ላይ የነበረው መንግሥት የኢትዮጵያን የወደብ ጉዳይ እና የባሕር በር መብት ሙሉ በሙሉ አሳልፎ በመስጠት ታሪካዊ ስህተት ፈፅሟል።
• በተጨማሪም የኢሕአዴግ መንግሥት በአልጀርስ ስምምነት ወቅት ተቀባይነት የሌላቸውን የቅኝ ግዛት ውሎች መሠረት በማድረግ ይህንን ህጋዊ እና ታሪካዊ መብቷን አላስከበረም።
• በአሁኑ ወቅት የኤርትራው አሰብ ወደብ የንግድ እንቅስቃሴ የማይታይበት "ጎስት ሲቲ" ሆኖ፣ እራሷን ኤርትራንም ሆነ የአካባቢውን ሀገራት ሳይጠቅም ቀርቷል።
የማይቀረው ትንሳኤ፡- ትውልዱ እና የውሃ በሩ
ኢትዮጵያ በዘመናት ታሪኳ ያጋጠሟትን እነዚህን ሁሉ ፖለቲካዊ፣ ታሪካዊ እና ጂኦ-ፖለቲካዊ መሰናክሎች አልፋ እና ተሻግራ የባሕር በር ባለቤትነቷን በእርግጠኝነት ታረጋግጣለች።
ያጣችውን ህጋዊ እና ታሪካዊ መብቷን በሰላማዊ፣ በዲፕሎማሲያዊ እና በማይናወጥ ጽናት መልሳ ታስከብራለች።
ኢትዮጵያ የቀጣናውን ሰላም በማረጋገጥ ከጎረቤት ሀገራት ጋር በመደመር፣ በጋራ ተጠቃሚነት እና በሰጥቶ መቀበል የትብብር መርህ በጋራ ለመሥራት ሁሌም ዝግጁ ናት።
ለዚህ ታላቅ ሀገራዊ እና ኅልውናዊ ዓላማ ደግሞ፣ የዛሬው ትውልድ ከመቼም ጊዜ በበለጠ ነቅቶ ተነስቷል። በእልህ እና በቁርጠኝነት የኢትዮጵያን የውሃ በር ጥያቄ ከዳር ሳያደርስ፣ መልህቋንም በክብር ሳይጥል አያርፍም!
በአዶኒያስ ወልደአረጋይ
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: