Search

ኢትዮጵያ COP32ን ማዘጋጀቷ ለአረንጓዴ ኢኮኖሚ ያላትን ቁርጠኝነት የሚያረጋግጥ ነው - ፕላንና ልማት ሚኒስቴር

ሓሙስ ሐምሌ 30, 2018 46

ኢትዮጵያ 32ኛውን የዓለም የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ (COP32) ማዘጋጀቷ ለአረንጓዴ ኢኮኖሚ ልማት ያላትን ቁርጠኝነት ይበልጥ የምታረጋግጥበት መሆኑ ተገልጿል።

የፕላን እና ልማት ሚኒስቴር አመራሮች እና ሠራተኞች ጉባኤውን ምክንያት በማድረግ በምሥራቅ ሸዋ ዞን በተለየ 7 ሄክታር መሬት ላይ የአረንጓዴ አሻራቸውን አሳርፈዋል።

በመርሐ ግብሩ ላይ በሺዎች የሚቆጠሩ የፍራፍሬ ችግኞች የተተከሉ ሲሆን እነዚህም አርሶ አደሩን በቀጥታ የኢኮኖሚ ተጠቃሚ የሚያደርጉ መሆናቸው ተጠቅሷል።

የፕላን እና ልማት ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ስዩም መኮንን እንደገለጹት ይህ ተግባር የአየር ንብረት ለውጥን ከመከላከል ባለፈ የምግብ ዋስትናን በማረጋገጥ ረገድ የራሱን አዎንታዊ ዐሻራ ያስቀምጣል።

የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር የአየር ንብረት ለውጥን በመቋቋም እንዲሁም የአፈርና የውኃ ሀብት ጥበቃን በማጠናከር ዘርፈ ብዙ የኢኮኖሚ ፋይዳ እያስገኘ መሆኑንም ሚኒስትር ዴኤታው ተናግረዋል።

በአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር እየታየ ያለው የሕዝብ ከፍተኛ ተሳትፎም አብሮነትን እና አንድነትን በማጠናከር ሀገራዊ የልማት ባህል እንዲሆን ማስቻሉን አክለዋል።

ኢትዮጵያ የኮፕ 32 አዘጋጅ መሆኗ የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ልማት ሥራዎቿን በማስቀጠል ለዘርፉ ያላትን ጠንካራ ቁርጠኝነት በተግባር የምታሳይበት መድረክ መሆኑ ተብራርቷል።

በሙሉ ግርማይ

 

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: