ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በኢትዮጵያ ከቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ቀጥሎ ሁለተኛውን ግዙፍ የሆነውን የባሕር ዳር ደጃዝማች በላይ ዘለቀ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ አዲሱ ተርሚናልን በባሕር ዳር ከተማ መርቀው ከፍተዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በምረቃ ሥነ-ሥርዓቱ ላይ ባደረጉት ንግግር፣ ባሕር ዳር ከተፈጥሮ ፀጋዋ በተጨማሪ የኢትዮጵያ እና የአፍሪካ የልማት እንዲሁም የብልጽግና ምሳሌ መሆን የምትችል ታሪክ ጠገብ ከተማ መሆኗን ገልጸዋል።
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በቱሪዝም፣ በኢንዱስትሪ ፓርክ ግንባታ፣ በውስጥ ለውስጥ መንገዶች፣ በግዙፉ የዓባይ ድልድይ እና በኮሪደር ልማት ከተማዋ ከፍተኛ መነቃቃት ውስጥ መሆኗን ጠቅላይ ሚኒስትሩ አብራርተዋል።
የዛሬው ግዙፍ የአውሮፕላን ማረፊያ ግንባታም ቀድሞ የነበረው አሮጌ ተርሚናል በግጭት ምክንያት መመታቱን ተከትሎ ችግሩን ወደ መልካም እድል በመቀየር ለትውልድ የሚሻገር የተሻለና ያማረ ፕሮጀክት ዕውን ማድረግ መቻሉን አውስተዋል።
አያይዘውም የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፍትህን ለማረጋገጥ ቴክኖሎጂን በመጠቀም የጀመረውን የቨርቹዋል ችሎት አሠራር በአብነት አንስተው አድንቀዋል።
ከዚህ ግዙፍ የልማት ሥራ ጎን ለጎን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ለክልሉ ሕዝብና አመራር ሁለት ቁልፍ መልዕክቶችን አስተላልፈዋል።
የከተማዋን ገቢ ማሳደግ ሲሆን፣ ባሕር ዳር ይህን ሁሉ ግዙፍ መሰረተ ልማት ይዛ በሀገር አቀፍ ደረጃ በገቢ አሰባሰብ ሰባተኛ ደረጃ ላይ መገኘቷ የተሰሩትን ፕሮጀክቶች እንኳን ለመጠገን አቅም የሚያሳጣ በመሆኑ ነዋሪውና አመራሩ በልዩ ትኩረት ሊሰራበት እንደሚገባ አሳስበዋል።
ዋነኛው ጠንካራ መልዕክታቸው ደግሞ የሰላም ጉዳይ ነው። ጠቅላይ ሚኒስትሩ አንደኛው ልጅ ጥሮ ግሮ ሲያመጣ ሌላኛው እንደሚያጠፋበት እናት ተምሳሌታዊ ታሪክ በመጥቀስ፣ "ቀኙ የሰራውን ግራ እያፈረሰው" የሚለውን ብሂል በማንሳት ያገኘነውን እድል በልማት እንድንጠቀምበት አሳስበዋል።
ልማትን ለማስቀጠል ሰላምን ማስቀደም ወሳኝ መሆኑን አስገንዝበው፣ ቀኙ ግራውን ማሳረፍ ካልቻለ የተጀመሩ የልማት ተስፋዎች ሊበላሹ እንደሚችሉ አስጠንቅቀዋል።
አሁን ላይ ክልሉ ራሱን በራሱ በተሟላ ሁኔታ እያስተዳደረ መሆኑን በመጠቆም፣ ሕዝቡ በጋራ በመቆም ከተማዋንና ክልሉን እንዲያለማ ጥሪ አቅርበዋል።
አለመግባባቶች ቢኖሩ እንኳ ዘመን ሳያልፍብን በጨዋነት እና በንግግር የመፍታት ባህልን ማዳበር እንደሚገባ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በመልዕክታቸው አስገንዝበዋል።
በለሚ ታደሰ
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: