አንዳንዶች "ኢትዮጵያውያን እርስ በርሳቸው መመካከር አይችሉም፤ የሐሳብ ልውውጥ ቋንቋቸው የጠመንጃ አፈሙዝ ብቻ ነው" የሚል የተሳሳተ እና ከእውነት የራቀ ትርክት ሲያራምዱ ይደመጣሉ።
እውነታው ግን ከዚህ ፍጹም ተቃራኒ ነው። ኢትዮጵያውያን ዛሬ በአጋጣሚ ሳይሆን፣ ከጥንት አባቶቻቸው ጀምሮ ቆም ብለው መነጋገር፣ መመካከር እና የቱን ያህል የሰፉ ልዩነቶችን እንኳ በሰከነ ውይይት መፍታት የሚችሉ ታላቅ ሕዝቦች ናቸው። ይህንን አኩሪ ማንነት ለመረዳት የውይይት እና የዕርቅ ማኅደር የሆነውን ታሪካችንን መመልከት በቂ ነው።
በመሠረቱ፣ ኢትዮጵያውያን በውስጣቸው ጥልቅ የሆነ ቁጭ ብሎ የመመካከር የሰጥቶ መቀበል ዕሳቤን ያዘሉ የሠለጠኑ ሕዝቦች ናቸው። ለዚህም በአፍሪካ ቀንድ የዴሞክራሲ፣ የእኩልነት እና የውይይት ተምሳሌት የሆነውን ጥንታዊውን የገዳ ሥርዓት ማንሳት ይቻላል።
በተመሳሳይ፣ በአማራው ማኅበረሰብ ውስጥ ጠለቅ ያለ የሽምግልና፣ ዛፍ ሥር ተቀምጦ ጉዳዮችን የመመካከር እና የዕርቅ ባሕላዊ ዕሴቶች በስፋት አሉ። ወደ ደቡብ የሀገራችን ክፍል ስንጓዝም፣ ማኅበረሰቡ ችግሮቹን በጋራ የሚፈታባቸው እና ውሳኔ የሚያሳልፍባቸው እንደ "ቡጫ ወጋ" እና "ዱቡሻ" የመሳሰሉ ልዩ ልዩ ዴሞክራሲያዊ የውይይት አደባባዮች አሉን።
እነዚህ አንጸባራቂ ዕሴቶች የሚያሳዩት፣ ሕዝባችን ልዩነትን በውይይት የማረቅ፣ የመደማመጥ እና በጋራ መግባባት ላይ የመድረስ የዳበረ የፖለቲካ እና የማኅበራዊ መስተጋብር ባሕል ያለው መሆኑን ነው።
የኢትዮጵያውያን የምክክር ማዕከል እና የውይይት ማዕዘን ሁሌም "ኢትዮጵያ" ናት። ማዕዘኑን በማጠናከር፣ አንድነትን በማጽናት እና ሀገርን በማስቀጠል ላይ ያተኮረ ውይይት እንጂ፣ "እኔ ያልኩት ካልሆነ" (My way or the highway) የሚል አግላይ ዕሳቤ በእውነተኛው የኢትዮጵያውያን ዕሴት ውስጥ ቦታ የለውም። ምክንያቱም፣ በሀገር ግንባታ ሒደት ውስጥ ሕዝባችን የሚፈልገው የአንዱን ሞት እና የሌላውን አሸናፊነት ሳይሆን፣ ፍጹም "የጋራ አሸናፊነትን" ነው።
ከዚህ ቀደም ለዘመናት ሀገርን ሲያደማ የነበረው የአሸናፊ እና ተሸናፊነት የፖለቲካ ትርክት የተናቀቀው እና የተሰበረውም፣ የጋራ አሸናፊነትን በሚያነግሠው በዚህ ብስለት የተሞላበት የምክክር ጥበብ ነው።
ውይይት በራሱ የረቀቀ ጥበብ እና ሳይንሳዊ ሒደት ነው። በዚህ ጥበብ ውስጥ የተለየ ሐሳብ ያለውን ወገን በጽሞና ማዳመጥ፣ ስሜቱን እና ጥያቄውን በጥልቀት መረዳት፣ እና በመጨረሻም የጋራ አማካይን (Golden mean) በጥበብ የመፈለግ ታጋሽነት አለ።
የኢትዮጵያ የጥንት አባቶች ይህንን የሰጥቶ መቀበል ጥበብ በሚገባ ተክነውት እና ኖረውት አልፈዋል። ዛሬም የነዚሁ አባቶች ልጆች፣ ያንን ጥንታዊ ጥበብ ከዘመኑ የዴሞክራሲ ዕሳቤ ጋር አዋህደው በአዳራሽ ውስጥ ተሰብስበው ሀገራዊ ምክክር እያደረጉ ይገኛሉ።
በምክክር አዳራሹ ውስጥ ተሳታፊዎች ይነጋገራሉ፣ ይከራከራሉ፣ ሐሳብን በሐሳብ ይሞግታሉ። ይህ ደግሞ እጅግ ጤናማ የሆነ እና የሚበረታታ የዴሞክራሲ ልምምድ ነው።
እያንዳንዱ ወገን "የእኔ ሐሳብ ትክክል ነው፣ መፍትሔም ያመጣል" ብሎ አጥብቆ ሊከራከር ይችላል፤ ነገር ግን በመጨረሻ በሐሳቦቻቸው መካከል የተፈጠሩ ልዩነቶችን እና የተራራቁ ጠርዞችን በጥበብ ያጠብባሉ።
አልደማመጥም፣ አልነጋገርም፣ እኔ ያልኩት ብቻ በጉልበት ይፈጸም ማለት የኢትዮጵያውያን ወግ፣ የባሕል መገለጫ ወይም የአባቶች ውርስ አይደለም።
ከእውነተኛ ማንነታችን እና ከተከበረው ዕሴታችን የወረስነው ተግባርም አይደለም። አሁን ላይ ኢትዮጵያውያን ይህንን እንግዳ እና አፍራሽ ባሕል አሸንፈው እየወጡ ይገኛሉ።
በአዶኒያስ ወልደአረጋይ
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: