በኢትዮጵያ ዘመናዊ የፖለቲካ ታሪክ ውስጥ ትልቁ የመዋቅራዊ ቀውስ እና የዕድገት ማቆልቆያ ምንጭ የፖለቲካ ኃይሎች ዋልታ-ረገጥ አቋም እና የ"አሸናፊ-ተሸናፊ" የፖለቲካ ባህል ነው።
በዚህ የስሌት መንገድ የአንድ ወገን ማሸነፍ የግድ የሌላው ወገን መሸነፍ ወይም መገለል ተደርጎ ስለሚወሰድ፣ ሀገራችን ለዘመናት በእርስ በእርስ ግጭት እና በፖለቲካዊ ውጥንቅጥ ውስጥ እንድትቆይ ምክንያት ሆኗል።
ይህንን አደገኛ የፖለቲካ አዙሪት በመስበር ወደ አማካዩ እና አካታቹ መንገድ ለመሸጋገር፣ በአዋጅ ቁጥር 1265/2014 የተቋቋመው የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ያሰናዳው እና 4 ሺህ ተወካዮችን እያሳተፈው ያለው ዋናው የምክክር ጉባኤ የተከፈተ ትልቅ ሀገራዊ ተስፋ ነው።
ከ"አሸናፊ-ተሸናፊ" ስሌት ወደ የጋራ መግባባት
አማካዩን ፍለጋ የአቋም አልቦነት የፖለቲካ ፍልስፍናን፣ ጽንፈኝነትን እና ጥላቻን አስወግዶ ጥልቅ አስተሳሰብ ባለው መካከለኛ መንገድ ሀገራዊ መግባባትን የመገንባት ስትራቴጂያዊ ጥረት ነው።
ሀገራዊ ምክክሩ እያካሄደው ያለው ጉባኤ አሸናፊ እና ተሸናፊ የሚለይበት የምርጫ ውድድር ወይም የኃይል ፍልሚያ አይደለም። ይልቁንም ከመላ ሀገራችን የተሰበሰቡ 8 ዋና ዋና አጀንዳዎችን በመክፈት ታሪካዊ እና መዋቅራዊ ቅሬታዎችን በውይይት ለመፍታት የተዘጋጀ መድረክ ነው።
ሂደቱ የፖለቲካ ጥያቄዎች በጠብመንጃ አፍ ሳይሆን በምክክር እንዲመለሱ በማድረግ፣ የኢትዮጵያን የፖለቲካ ምኅዳር ከጥላቻ እና ከመጠፋፋት ወደ አብሮነት እና አካታችነት ያሸጋግረዋል።
የኢትዮጵያ መጻኢ ተስፋ
ሀገራዊ እና ዓለም አቀፋዊ እውነታዎች የሚያሳዩት፣ ምንም ያህል የከረረ የፖለቲካ ልዩነት ቢኖር እንኳ በመደማመጥ እና በመከባበር "አማካይ መፍትሔ" ማግኘት እንደሚቻል ነው። ይህ የሚቻለው ደግሞ ሀገር ከምንም የላቀች መሆኗን በማሰብ የግል እና ቡድን ፍላጎትን ለሀገር በማስገዛት የሚመጣ ነው።
የደቡብ አፍሪካ፣ ቱኒዝያ፣ አየር ላንድ እና ኮሎምቢያን የመሳሰሉ ሀገራት ተሞክሮዎች እንደሚያሳዩት ምክክሮች በአብዛኛው በፖለቲካ ልሂቃን መካከል የተደረጉ ድርድሮች ናቸው፤ የኢትዮጵያው ግን በተቃራኒው የሁሉንም ማኅበረሰብ ክፍል ያካተተ ሰፊ መሠረት ያለው ምክክር ነው።
ከ1 ሺህ 200 በላይ ወረዳዎች እና ከ200 ሺህ በላይ ዜጎች የተሳተፉበት የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ሂደት፣ ከተጠቀሱት ሁሉ በተለየ መልኩ በየደረጃው ያለውን ማኅበረሰብ በቀጥታ ያሳተፈ ነው።
በቀጣይም በምክክሩ የሚደረሱ ስምምነቶችን በተግባር በመተርጎም እና የሕዝብ ባለቤትነትን በማረጋገጥ ኢትዮጵያን ወደ አዲስ የታሪክ፣ የሰላም እና የዴሞክራሲ ምዕራፍ ማሸጋገር ይቻላል።
ሀገርን የሚያስቀድም እና ለትውልድ የሚያስብ ወገን ሁሉ ይህን ወርቃማ ዕድል የመጠቀም ታላቅ ኃላፊነት ተጥሎበታል።
በለሚ ታደሰ
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: