Search

የባሕር በር ማጣት፡- የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ እየፈተነ ያለው ትልቁ ማነቆ

ዓርብ ሐምሌ 17, 2018 122

ኢትዮጵያ በቆዳ ስፋቷና በሕዝብ ብዛቷ በምሥራቅ አፍሪካ ግዙፍ፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ ደግሞ ፈጣን እድገት እያስመዘገቡ ካሉ ሀገራት አንዷ ናት። ሆኖም ይህን እምቅ አቅሟን ሙሉ በሙሉ ተጥቀማ በዓለም አቀፍ መድረክ ተወዳዳሪና የላቀች ሀገር እንዳትሆን ከፊቷ የተደቀነባት ትልቅ ፈተና አለ። ይህም የራሷ የባሕር በር አለመኖር ነው።

በዛሬው የዲጂታል እና የነፃ ገበያ ዓለም፣ የአንድ ሀገር የኢኮኖሚ ጥንካሬ የሚለካው ከዓለም አቀፍ ገበያ ጋር ባለው ትስስር ነው። ኢትዮጵያ የወጪና ገቢ ንግድ ዕቃዎችን ለማጓጓዝ በጎረቤት ሀገራት ወደቦች ላይ ሙሉ በሙሉ ጥገኛ እንድትሆን ያስገደደው የባሕር በር አልባነት፣ ሀገራችን በየዓመቱ ለወደብ ኪራይና ለሎጂስቲክስ አገልግሎት እጅግ ከፍተኛ የሆነ የውጭ ምንዛሪ እንዲታወጣ አስገድዷታል።

ከኢትዮጵያ ወደ ውጭ የሚላኩ ምርቶች እንደ ቡና፣ የሰሊጥ፣ የጨርቃጨርቅ እና ሌሎች ምርቶች በሎጂስቲክስ ወጪ ምክንያት በዓለም አቀፍ ገበያ ላይ ያላቸው ዋጋ ውድ ስለሚሆን ተወዳዳሪነታቸው እንዲቀንስም የራሱ የሆነ አሉታዊ ሚና ተጫውቷል።

ግዙፍ የዓለም አቀፍ ኩባንያዎች ኢንቨስት ለማድረግ ሲያስቡ ከሚመለከቷቸው ዋና ዋና ነገሮች አንዱ የሎጂስቲክስ ቅልጥፍና ነው። ወደብ የሌላቸው ሀገራት ጥሬ ዕቃዎችን ለማስገባትም ሆነ ያለቀላቸውን ምርቶች ወደ ዓለም ገበያ ለመላክ ጊዜና ገንዘብ ስለሚጠይቅ፣ ኢንቨስተሮች ወደቦች ወዳሏቸው ሀገራት የመሳብ ዕድላቸው ከፍተኛ ነው።

እንዲሁም የባሕር በር አለመኖር የኢኮኖሚ ጉዳይ ብቻ ሳይሆን፣ የሀገራዊ ደኅንነትና የስትራቴጂያዊ ነፃነት ጉዳይም ነው። የንግድ መስመሮች በጎረቤት ሀገራት ፖሊሲ፣ መረጋጋትና ፍላጎት ላይ ጥገኛ ሲሆኑ፣ ሀገር በድንገተኛ አደጋዎች ወቅት ተጋላጭነቷ ይጨምራል።

የባህር በር አለመኖር ትልቅ ማነቆ ቢሆንም፣ ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪነቷን ለማረጋገጥ የዲፕሎማሲና አማራጭ ወደቦች አጠቃቀም ላይ ትኩረት በማድረግ ከተለያዩ የጎረቤት ሀገራት ጋር በመነጋገር የባሕር በር አማራጮችን ለማስፋትና በፍትሃዊ መንገድ የመጠቀም መብትን ለማረጋገጥ እየሰራች ትገኛለች።

በአድማሱ አራጋው

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: