ዲጂታል ቴክኖሎጂ እና የአየር ንብረት ጥበቃ በተቀናጀ መንገድ ሲራመዱ አዳዲስና ተስፋ ሰጪ የኢኮኖሚ እድሎችን ይዘው ብቅ ይላሉ፤ ከእነዚህም መካከል የካርቦን ንግድ ዋነኛው ነው።
ይህን እንቅስቃሴ በዲጂታል ሥርዓት መደገፍ ደግሞ የሥራውን ግልጽነት፣ የፍጥነት አቅምና የዓለም አቀፍ ገበያ ተደራሽነትን በከፍተኛ ደረጃ እንደሚያሳድገው ጥናቶች ያረጋግጣሉ።
ሀገራችን ኢትዮጵያ በአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብሯ ቢሊዮን ችግኞችን በመትከል ካርቦንን ከአየር ላይ ስቦ የማስቀረት (Carbon Sequestration) አቅሟን በእጅጉ እያሳደገች ትገኛለች። ይህ የተገነባ የተፈጥሮ ሀብት በዘመናዊ መንገድ ተመዝግቦ፣ ተረጋግጦና ተሰናድቶ በዓለም አቀፍ የዲጂታል ካርቦን ገበያ ላይ ሲቀርብ ለኢትዮጵያ ተጨማሪና ዘላቂ የሆነ የውጭ ምንዛሬ ምንጭ ሆኖ ያገለግላል።
የዲጂታል ካርቦን ንግድ ዝግጅት የሚከናወነው የካርቦን ቅነሳ ሂደቱን በሳተላይት፣ በጂኦግራፊያዊ መረጃ ሥርዓት፣ በርቀት ዳሰሳ (Remote Sensing) እና በዘመናዊ ዲጂታል መረጃ ቋቶች በመመዝገብ፣ በመከታተልና በማረጋገጥ ነው። ይህም አሰራር ዓለም አቀፍ የካርቦን ገበያ የሚፈልጋቸውን ጥብቅ መስፈርቶች ሙሉ በሙሉ ለማሟላት፣ የመረጃ አስተማማኝነትን ለማረጋገጥ እና የዓለም አቀፍ ኢንቨስተሮችን እምነት ለማጠናከር ያስችላል።
በተጨማሪም ይህ የቴክኖሎጂ ዝግጅት ከአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብር ባሻገር የደን ጥበቃን፣ የእርሻ መሬት አስተዳደርን፣ የታዳሽ ኃይል ፕሮጀክቶችንና የንጹህ ማብሰያ ቴክኖሎጂዎችን የሚያካትት በመሆኑ፣ በእነዚህ ዘርፎች የሚመነጨውን የካርቦን ቅነሳ ማረጋገጫ (Carbon Credit) በቀጥታ ወደ ዓለም አቀፍ ገበያ ለማስገባት ጠንካራ መሠረት ይጥላል።
የዲጂታል ካርቦን ንግዱ ኢትዮጵያ በአፍሪካ አረንጓዴ ኢኮኖሚን ለመገንባት የያዘችውን ራዕይ ያፋጥነዋል።ይህም ተፈጥሮን በመንከባከብና በመጠበቅ ብቻ ገቢ የሚገኝበት፣ ዛፍ የአካባቢ ጥበቃ መጠቀሚያ ብቻ ሳይሆን እውነተኛ የኢኮኖሚ ሀብት የሚሆንበትን አዲስ የዕድገት ምዕራፍ ይከፍታል።
በአጠቃላይ የዲጂታል ካርቦን ንግድ ዝግጅት ተራ የቴክኖሎጂ ፕሮጀክት ሳይሆን፣ የኢትዮጵያን አረንጓዴ ልማት ከዓለም አቀፍ ኢኮኖሚ ጋር የሚያ አስተሳስርና የተፈጥሮ ሀብቷን ወደ ዘላቂ ገቢ የሚቀይር ስትራቴጂያዊ ርምጃ ነው። አረንጓዴ ሀብታችን በዲጂታል መድረኮች ሲመዘገብና በዓለም ገበያ ተገቢውን ዋጋ ሲያገኝ፣ ሀገራችን ተፈጥሮዋን ጠብቃ ኢኮኖሚዋን የምታሳድግበት አዲስና ብሩህ መንገድ ይከፈታል።
በልዩ እሸቱ
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: