Search

ምክር ቤቱ የሕዝቡን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ሲሠራ ቆይቷል - ምክትል አፈ ጉባኤ ወ/ሮ ወላይቴ ቢቶ

ዓርብ ሐምሌ 17, 2018 105

የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ምክር ቤት 6ኛ ዙር፣ 5ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 7ኛ መደበኛ ጉባኤውን በአርባ ምንጭ ከተማ ማካሄድ ጀምሯል።

የክልሉ ምክር ቤት ምክትል አፈ-ጉባኤ ወ/ሮ ወላይቴ ቢቶ በጉባኤው መክፈቻ ላይ ባስተላለፉት መልዕክት፣ ምክር ቤቱ ባለፉት ዓመታት ከሕዝቡ የተቀበለውን አደራ በሙሉ አቅሙ በመወጣት የሕዝቡን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ሲሠራ መቆየቱን ገልጸዋል።

ጉባኤው 7ኛው ሀገራዊ ምርጫ በስኬት በተጠናቀቀ ማግስት የሚካሄድ መሆኑን ጠቅሰው፣ ምርጫውን ተከትሎ አዲስ መንግሥት ለመመስረት ዝግጅት እየተደረገ ባለበት እንዲሁም ኢትዮጵያ የዘመናት ስብራቶቿን በውይይት ለመጠገን ሀገራዊ የምክክር ጉባኤ በሚካሄድበት ወቅት የተዘጋጀ ወሳኝና ታሪካዊ መድረክ መሆኑን አስረድተዋል።

በበጀት ዓመቱ ምክር ቤቱ በአስፈጻሚ አካላት ላይ ያደረገውን የድጋፍና ቁጥጥር ሥራ በማጠናከር፣ የተቋማትን የመፈጸምና የማስፈጸም አቅም ለማዳበር ውጤታማ ሥራዎች መከናወናቸውን ጠቁመዋል።

የተሻለ አፈጻጸም ላስመዘገቡ ተቋማት ዕውቅና የመስጠትና ክፍተት የተስተዋለባቸውን የማረም ሥራ መሠራቱንም አብራርተዋል።

በጉባኤው የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ጥላሁን ከበደ የክልሉን መንግሥት የ2018 በጀት ዓመት አጠቃላይ የሥራ አፈጻጸም ሪፖርት አቅርበው፣ ከምክር ቤቱ አባላት ለሚነሱ ጥያቄዎችና አስተያየቶች ምላሽና ማብራሪያ የሚሰጡ ይሆናል።

በተጨማሪም ምክር ቤቱ በክልሉ መንግሥት የ2019 ዓ.ም የበጀት አዋጅ ረቂቅ ላይ በሰፊው መክሮ ያጸድቃል ተብሎ ይጠበቃል።

ዛሬን ጨምሮ ለተከታታይ ሁለት ቀናት በሚካሄደው ጉባኤ፣ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ጥላሁን ከበደ፣ የምክር ቤት አባላት እና ጥሪ የተደረገላቸው ተጋባዥ እንግዶች ተገኝተዋል።

በትዕግስቱ ቡቼ

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: