ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ የኢትዮጵያን የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ጉዞ ወደ ላቀ ደረጃ የሚያሸጋግረው "ፋይዳቨርስ" በይፋ ሥራ መጀመሩን አስመልክተው መልዕክት አስተላልፈዋል።
በመልዕክታቸውም፣ ባለፉት ጥቂት ዓመታት የብሔራዊ ዲጂታል መታወቂያ ፕሮግራም ወደ 50 ሚሊዮን የሚጠጉ ዜጎችን በመመዝገብ፣ ከ160 ሚሊዮን በላይ የማረጋገጫ አገልግሎቶችን በመስጠት እና የፋይናንስ አካታችነትን በማረጋገጥ የዲጂታል ኢኮኖሚው የጀርባ አጥንት መሆኑን በተግባር ማስመስከሩን ገልጸዋል።
ይህንኑ ስኬት ወደ ቀጣዩ ምዕራፍ ለማሸጋገር ተቋሙ በኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ ስር "ፋይዳቨርስ" በሚል ስያሜ ራሱን የቻለ የመንግሥት የልማት ድርጅት በመሆን ወደ ሥራ መግባቱን አብራርተዋል።
ይህ ውሳኔ ዲጂታል ማንነት ልክ እንደ መንገድ፣ ኃይል እና ቴሌኮሙኒኬሽን ሁሉ ለሀገራችን ተወዳዳሪነት እና ዘላቂ ዕድገት ወሳኝ የሆነ ስትራቴጂያዊ ሀገራዊ መሰረተ ልማት ለመሆኑ ማረጋገጫ ነው ብለዋል ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን።
ተቋሙ ከሀገር አልፎ በዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ስትራቴጂ መሰረት ለቀጣናው እና ለአፍሪካ አህጉር ልምድ እና አቅም በማጋራት ኢትዮጵያ የአፍሪካ የዲጂታል ሽግግር መሪ እንድትሆን እንደሚያስችላትም አክለው ገልጸዋል።
የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ጉዞ ስኬት የሚለካው በተደረሰባቸው ቴክኖሎጂዎች ሳይሆን፣ ሕዝቡ እነዚህን ውጤቶች የራሱ አድርጎ ሲጠቀምባቸው እና ሕይወቱ ሲለወጥ መሆኑን አንስተዋል።
መንግሥት የቴክኖሎጂ አቅርቦት ጥራትን በመጠበቅ፣ የዳታ ደኅንነትን በማረጋገጥ እና የዜጎችን ዲጂታል ግንዛቤ በማሳደግ የጀመረውን ሥራ በበለጠ ቁርጠኝነት አጠናክሮ እንደሚቀጥልም አረጋግጠዋል።
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: