ፕሬዚዳንት ታየ አጽቀ ሥላሴ የኢትዮጵያን ከፍተኛ ልዑካን በመምራት በኒውዮርክ እየተካሄደ ባለው የዓለም አቀፍ ታዳሽ ኃይል ጉባኤ ላይ እየተሳተፉ ነው፡፡
ፕሬዚዳንቱ በጉባኤው ላይ ባደረጉት ንግግር ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ የታዳሽ ኃይል ትኩረቱን ኃይል ከማመንጨት ባሻገር ኤሌክትሪክን ለኢኮኖሚያዊ ሽግግር ለማዋል ወደሚያስችሉ መሠረተ ልማቶች ሊያሸጋግር እንደሚገባ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
የኃይል ማስተላለፊያ መስመሮች፣ የኃይል ማከማቻዎች እና ጠንካራ የኤሌክትሪክ አቅርቦት አቅም ሳይኖሩ ማመንጨት ብቻውን የኢኮኖሚ ሽግግርን ስለማያመጣ አዳጊ ሀገራት እምቅ አቅማቸውን ወደ አስተማማኝ ተደራሽነት እና የኢንዱስትሪ ዕድገት እንዲቀይሩ ጠንካራ ዓለም አቀፍ የፋይናንስ ድጋፍ ያስፈልጋል ብለዋል፡፡
ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት ካላት 9 ሺህ 761 ሜጋ ዋት አቅም ውስጥ ከ95 በመቶ በላይ የሚሆነው ከታዳሽ ኃይል የሚገኝ መሆኑን ያብራሩት ፕሬዚዳንቱ፤ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ እና ሌሎች የኃይል ማመንጫዎች ለኤሌክትሪክ ተደራሽነት እና ኢንዱስትሪ ልማት መሠረት መሆናቸውን አስገንዝበዋል፡፡
ግድቡ በሀገር ውስጥ አቅም እና በሰፊ የሕዝብ ተሳትፎ መገንባቱ የሀገር በቀል ባለቤትነት ማሳያ መሆኑንም ጠቅሰዋል፡፡
በተጨማሪም መንግሥት በአሁኑ ወቅት በአስር ሺዎች የሚቆጠር ሜጋ ዋት እምቅ አቅምን ለመጠቀም ሦስት ዐበይት ጉዳዮች ላይ እያተኮረ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ይኸውም በፈረንጆቹ 2030 የማመንጨት አቅምን 14 ሺህ ሜጋ ዋት ማድረስ እንዲሁም ከውኃ ውጭ ያሉ የታዳሽ ኃይል ምንጮችን ድርሻ ወደ 15 በመቶ ማሳደግ፣ ንጹህ የኤሌክትሪክ ኃይልን ለኢንዱስትሪ ተወዳዳሪነት ማዋል እና የግል ዘርፉን በኃይል ማስተላለፍ እና ማከፋፈል ሥራ ለማሳተፍ የማክሮ ኢኮኖሚ እና የኢነርጂ ዘርፍ ማሻሻያዎችን መተግበር ናቸው፡፡
ለእነዚህ ሥራዎች የፋይናንስ አቅርቦት ወሳኝ መሆኑን ያነሱት ፕሬዚዳንቱ፤ የዓለም ባንክ፣ የአፍሪካ ልማት ባንክ እና የአውሮፓ ኅብረትን ጨምሮ ዓለም አቀፍ አጋሮች ለኃይል ማስተላለፊያ መሠረተ ልማቶች ዝመና ላደረጉት ድጋፍ አመስግነው በቀጣይም ፋይናንስ እንዲያደርጉ ጠይቀዋል፡፡
የታዳሽ ኃይል ኢንቨስትመንት በጥቂት የበለጸጉ አካባቢዎች ብቻ ከተወሰነ ዓለም አቀፉ የኢነርጂ ሽግግር እንደማይሳካም ገልጸዋል፡፡
ለታዳጊ ሀገራት ዋናው ግብ ከኃይል አቅም ወደ ተደራሽነት፣ ከዚያም ወደ ኢንዱስትሪ ልማት እና የሥራ ዕድል ፈጠራ መሸጋገር መሆኑን አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡
ኢትዮጵያ በፈረንጆቹ 2027 የዓለም አቀፉን የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ (COP32) በአዲስ አበባ ለማስተናገድ ዝግጅት እያደረገች መሆኑን የጠቆሙት ፕሬዚዳንት ታየ፤ ዓለም አቀፍ የአየር ንብረት እና የታዳሽ ኃይል ቃል ኪዳኖች በመላው አፍሪካ በተጨባጭ ተግባር ላይ እንዲውሉ ኢትዮጵያ በትኩረት እንደምትሠራ አረጋግጠዋል፡፡
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: