Search

ከኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ የተሻገረ ትርጉም ያለው የኩርሙክ ወርቅ ፋብሪካ

ሰኞ መስከረም 11, 2019 16

የማዕድን ክፍለ-ኢኮኖሚ ከጥሬ ሀብት ሻጭነት ወጥቶ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ዋና ምሰሶ የሚሆንበት ታሪካዊ መዋቅራዊ ሽግግር በተጨባጭ እየተረጋገጠ ይገኛል።

በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል፣ አሶሳ ዞን የሚገኘው የኩርሙክ የወርቅ ማዕድን ፕሮጀክት የዘመናዊ እና ግዙፍ የኢንዱስትሪ ደረጃ የወርቅ ማቀነባበሪያ ፋብሪካ ግንባታን በማጠናቀቅ ወደ ምርት ምዕራፍ መሸጋገሩ በዘርፉ አዲስ የታሪክ ምዕራፍ ከፍቷል።

500 ሚሊዮን ዶላር በላይ የወጣበት ይህ ግዙፍ ፕሮጀክት በጂኦሎጂካል ጥናቶች በተረጋገጠ ከፍተኛ የወርቅ ክምችት ላይ የተመሠረተ ነው።

ፋብሪካው በመጀመሪያዎቹ 4 ዓመታት በዓመት አማካይ 9 ሜትሪክ ቶን ወርቅ የማምረት አቅም ያለው ሲሆን፣ ይህም ሀገራዊ የወርቅ ኤክስፖርት ምርትን ከአሁኑ በሦስት እጥፍ ያሳድገዋል።

ይህም አሁን ባለው ዓለም አቀፍ የወርቅ ዋጋ ስሌት መሠረት በዓመት 1.2 ቢሊዮን ዶላር በላይ ገቢ ያስገኛል።

ፕሮጀክቱ ዝቅተኛ የኤሌክትሪክ ኃይል መጠቀሙ በዓለም አቀፍ ደረጃ ከፍተኛ ተወዳዳሪነትን ያጎናጽፈዋል።

የኩርሙክ ወርቅ ፋብሪካ ከውጭ ምንዛሬ ግኝት ኢኮኖሚያዊ ፋይዳው ባሻገር የቀጣናውን ሰላም እና ደኅንነት በማረጋገጥ ረገድ ያለው ሚና እጅግ ከፍተኛ ነው።

ፕሮጀክቱ በሚገኝበት የድንበር አካባቢ ከዚህ ቀደም ይካሄድ የነበረው ባህላዊ እና ሕገ-ወጥ የወርቅ ቁፋሮ ለኮንትሮባንድ ንግድ እና ለድንበር ተሻጋሪ ግጭቶች መንስኤ ሆኖ ቆይቷል።

ግዙፉ የኢንዱስትሪ ፋብሪካ ወደ ሥራ መግባቱ ሕገ-ወጥ የወርቅ ዝውውርን የሚያከስም ከመሆኑም በላይ ይፋዊ የግብይት እና ቁጥጥር ሥርዓት እንዲሰፍን ያደርጋል።

ለአካባቢው ነዋሪዎች ሰፊ የሥራ ዕድል መፈጠሩ እና የመሠረተ ልማቶች መስፋፋታቸው በማዕድን ሀብት ስም የሚፈጠሩ ግጭቶችን በማስቀረት የአካባቢውን ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ መረጋጋት ያጠናክራል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (/) እንደገለጹት የኢንዱስትሪ የወደፊት ጉዞ በሦስት ዋና ዋና ምሰሶዎች ማለትም እሴት በተጨመረበት ምርት፣ በንጹህ ኃይል እና በሕዝብ ብዛት አቅም ላይ የተመሠረተ ነው።

ይህንን ራዕይ ተግባራዊ ለማድረግ የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ የመራው የመጀመሪያው ግዙፍ የወርቅ ማጣሪያ ፋብሪካ ግንባታ በመጠናቀቅ ላይ ይገኛል።

በብሔራዊ ባንክ አዲስ መመሪያ መሠረት በሀገር ውስጥ የሚመረተው ወርቅ በሙሉ በጥሬው ወደ ውጭ መላኩ ቀርቶ በሀገር ውስጥ ተጣርቶ ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ የወርቅ አሞሌ እንዲሆን ይደረጋል።

ይህም የውጭ የግብይት የበላይነትን በማስቀረት እና "ኢትዮጵያ ታምርት" የሚለውን መርሐ ግብር በመደገፍ ሀገራዊ የወርቅ ምርትን በእጥፍ ለማሳደግ የተያዘውን ግብ ያፋጥነዋል።

ከዚህ በተጨማሪም ሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል የሚያስገነባው 200 ሚሊዮን ዶላር የወርቅ ማቀነባበሪያ ፋብሪካ የዚሁ ሀገራዊ ጥረት አካል ነው።

የማዕድን ዘርፉን እሴት የመጨመር ስትራቴጂ በወርቅ ላይ ብቻ የተገደበ ሳይሆን በሌሎች የኢንዱስትሪ ማዕድናት ላይም በተጨባጭ እየተተገበረ ይገኛል።

በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (/) የተጎበኘውና በሰዓት እስከ 200 ቶን የማቀነባበር አቅም ያለው የአርጆ የድንጋይ ከሰል ማቀነባበሪያ ፋብሪካ ሙሉ በሙሉ የሀገር ውስጥ ሀብትን በመጠቀም ከፍተኛ የሙቀት አቅም ያለው የታጠበ ከሰል ማቅረብ ጀምሯል።

ይህም የሲሚንቶ እና የብረት ፋብሪካዎች ከደቡብ አፍሪካ እና አውስትራሊያ ከሰል ለማስገባት በዓመት ያወጡት የነበረውን 220 ሚሊዮን እስከ 300 ሚሊዮን ዶላር የውጭ ምንዛሬ በሀገር ውስጥ ምርት ለመተካት አስችሏል።

በሌላ በኩል በዓመት ለብረት ገቢ ምርት የሚወጣውን 850 ሚሊዮን ዶላር ለማስቀረት በደቡብ ወሎ የሚገነባው 150 እስከ 200 ሚሊዮን ዶላር የሚፈጀው የብረት ማዕድን ማቀነባበሪያ እና የኦሮሚያ አይረን ኤንድ ስቲል ፕሮጀክቶች ተጨባጭ ማረጋገጫዎች ናቸው።

በተጨማሪም እንደ ሊቲየም እና ታንታለም ያሉ ቴክኖሎጂ-መር ማዕድናት በጥሬያቸው ወደ ውጭ እንዳይላኩ ማዕድን ሚኒስቴር ቁጥጥር እያደረገ ሲሆን፣ በከበሩ ድንጋዮች ዘርፍም የላፒዳሪ ቴክኖሎጂን በመጠቀም 2029 ከኦፓል፣ ኤመራልድ እና ሳፋየር የሚገኘውን ኤክስፖርት ገቢ ወደ 812.75 ሚሊዮን ዶላር ለማሳደግ ጥረት እየተደረገ ይገኛል።

የኩርሙክ ወርቅ ፋብሪካ ወደ ሥራ መግባት እና በከሰል፣ በብረት እንዲሁም በክቡር ድንጋዮች ላይ እየተወሰዱ ያሉ የእሴት ጭማሪ እርምጃዎች ኢትዮጵያ ከተፈጥሮ ሀብቷ የሚገባትን እውነተኛ ጥቅም እንድታገኝ የሚያስችሉ ናቸው።

በጥሬ ዕቃ ኤክስፖርት ላይ የተመሠረተውን የቆየ አሠራር በመቀየር በሀገር ውስጥ ማቀነባበር፣ የውጭ ምንዛሬን ማዳን፣ ሰፊ የሥራ ዕድል መፍጠር እና ሀገራዊ የኢንዱስትሪ መዋቅርን ማጠናከር የማዕድን ዘርፉን የኢኮኖሚ ምሰሶነት በጽኑ መሠረት ላይ እየተከለው ይገኛል።

በለሚ ታደሰ

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: