Search

በመሪዎቿ መቀያየር የማይለወጠው ዘመናትን የተሻገረው የግብፅ ሴራ

ዓርብ ነሐሴ 08, 2018 52

ዓባይ ለሰሜን ምሥራቅ እና ለአፍሪካ ቀንድ ሀገራት የሕይወት እና የኢኮኖሚ ደም ስር ቢሆንም፣ የዘመናት የጂኦ-ፖለቲካዊ ጦርነት እና የዲፕሎማሲ ፍጥጫ አውድማ መሆኑ አልቀረም።

የውኃው 85 በመቶ ምንጭ የሆነችው ኢትዮጵያ፣ አንዲት ጠብታ ለማታመነጨው ግብፅ ሁሌም እንደ ትልቅ የብሔራዊ ደህንነት ስጋት ትታያለች።

በካይሮ የፖለቲካ ጓዳዎች ውስጥ የኢትዮጵያ ሰላም መሆን እንደ ትልቅ አደጋ፣ መታመሷ ደግሞ እንደ ትልቅ ብስራት ይቆጠራል።

የግብፅ ስትራቴጂስቶች የዓባይን ውኃ ሙሉ በሙሉ ለመቆጣጠር ሲሉ ከጥንት እስከ ዛሬ ኢትዮጵያን ደካማ እና የተበታተነች አድርጎ የማቆየት ፖሊሲን በፅናት ይከተላሉ። የግብፅ ዋነኛ ፍላጎት "ሃይድሮ-ሄጂመኒ" ወይም የውሃ የበላይነትን ማረጋገጥ ነው።

በታሪክ እንደምንገነዘበው 19ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ኸዲቭ እስማኤል ፓሻ «ታላቋን ግብፅ» ለመገንባት ባለመው ቅዥት ኢትዮጵያን በወታደራዊ ኃይል ለመውረር ሞክሮ በጉንደት እና በጉራዕ ውጊያዎች ከባድ ሽንፈት ተከናንቧል።

1929 እና 1959 በተደረጉት የዓባይ ውኃ ክፍፍል ስምምነቶችም ግብፅ የኢትዮጵያን ተፈጥሯዊ መብት ለመንፈግ ጥራለች።

በተለይ 1959 ስምምነት ኢትዮጵያ የውኃው ምንጭ ሆና ሳለ ድርሻዋ ዜሮ ሲደረግ፣ ግብፅ ግን 55.5 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር ድርሻን ለራሷ አፅድቃለች። ይህም የግብፅን ራስ ወዳድ ፖሊሲ እና የብቸኛ በላይነት ፍላጎት ፍንትው አድርጎ ያሳያል።

የግብፅ መሪዎች ቢቀያየሩም በኢትዮጵያ ላይ ያላቸው ጂኦ-ፖለቲካዊ አቋም ፈጽሞ አይቀየርም። ገማል አብዱል ናስር የኤርትራ አማፂያንን በማስታጠቅና ሶማሊያን በመደገፍ ኢትዮጵያ እንድትታመስ ሰርቷል። አንዋር ሳዳት በኦጋዴን ጦርነት ወቅት ለዚያድ ባሬ መንግሥት ዘመናዊ የጦር መሳሪያ አቅርቧል።

ሁስኒ ሙባረክ ኢትዮጵያ ለዓባይ ልማት ብድር እንዳታገኝ የቪቶ ተፅዕኖ አሳርፏል። አብዱልፈታህ አልሲሲ ደግሞ የሕዳሴ ግድብ ግንባታ ከተጀመረ በኋላ ኢትዮጵያን በዲፕሎማሲ ጫና እና በደህንነት ስጋት ለማንበርከክ ሌት ተቀን እየሠራ ይገኛል።

ግብፅ በቀጥታ ጦርነት ውስጥ ከመግባት ይልቅ በኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ የፖለቲካ እና የብሔር ኃይሎችን ለውክልና ጦርነት (Proxy War) በመጠቀም ሀገሪቱን የማዳከም ስትራቴጂ ትከተላለች።

በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ የውስጥ ግጭቷን በዘላቂነት ለመፍታት የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን አቋቁማ ወደ ሥራ መግባቷ ካይሮን እንቅልፍ የነሳ ጉዳይ ሆኗል።

ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ ልዩነቶች በምክክር ከተፈቱ የጠመንጃ ድምፅ ለዘለዓለም ይጠፋል፤ ይህ ማለት ደግሞ ሀገሪቱ ሙሉ አቅሟን፣ ጉልበቷን እና በጀቷን ወደ ልማት ታዞራለች ማለት ነው።

ይህ የግብፅን ዘመናትን የተሻገረ ስትራቴጂ ስለሚያፈርሰው፣ ምክክሩን ለማደናቀፍ የታጠቁ ኃይሎችን በመደገፍ እና በሚዲያዎቿ ፕሮፓጋንዳ በመንዛት ኢትዮጵያውያን በራሳቸው የፈውስ ሂደት ላይ ተስፋ እንዲቆርጡ እየሠራች ነው።

እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ሊገነዘበው የሚገባ ትልቅ ሐቅ አለ፤ በሀገር ውስጥ የሚያጋጥም እያንዳንዱ የብሔር ግጭት እና የጥይት ተኩስ ቀጥተኛ ትርፉ ለታሪካዊ ጠላቶቻችን ነው።

የካይሮ ፖለቲከኞች ሻያቸውን እየጠጡ የዓባይን ውኃ በብቸኝነት እንዲጠቀሙ መፍቀድ የለብንም።

ሀገራዊ ምክክሩ የፖለቲካ ልሂቃን ብቻ ጉዳይ ሳይሆን የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት ከውጭ አሻጥር የመታደግ ብሔራዊ አጀንዳ ነው።

የጠላቶቻችንን ሴራ ማክሸፍ የምንችለው መሳሪያን አውርደን ልዩነቶቻችንን ወደ ምክክር ጠረጴዛ ስናመጣቸው ብቻ ነው።

በሲሳይ ደበበ

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: