የኢትዮጵያ የባሕር በር ጥያቄ ከታሪካዊ ትርክቶች ባሻገር ዛሬ ላይ አንገብጋቢ የህልውና ጉዳይ ሆኗል።
ኢትዮጵያ ከ130 ሚሊዮን በላይ ዜጎች በሚኖሩባት እና የከተሜነት ምጣኔዋ በፍጥነት እያሻቀበ ባለበት በዚህ ወቅት፣ በኢኮኖሚ እያደረገችው ያለው መዋቅራዊ ሽግግር ከዓለም ገበያ ጋር ያላትን የንግድ እና የሀብት ፍሰት ፍላጎት በከፍተኛ ደረጃ አሳድጎታል።
ይህ ፈጣን የሥነ-ሕዝብ እና የኢኮኖሚ ዕድገት አሁን ባለው ውስን የገቢ እና ወጪ ንግድ መስመር አቅም ሊስተናገድ የሚችል ባለመሆኑ አስተማማኝ የባሕር በር ማግኘት ወደ ጂኦ-ፖለቲካዊ ብሔራዊ ደኅንነት ግዴታነት እየተሸጋገረ ይገኛል።
በቀጣዮቹ ሁለት አስርት ዓመታት የኢትዮጵያ ሕዝብ ቁጥር ከ150 ሚሊዮን እንደሚሻገር ዓለም አቀፍ እና ሀገራዊ የሥነ-ሕዝብ ትንበያዎች የሚያሳዩ ሲሆን፤ ይህ ግዙፍ ሀገር እና ሕዝብ የሚኖረው የምግብ ዋስትና፣ የኃይል፣ የነዳጅ እና የኢንዱስትሪ ማምረቻ ግብዓት ፍላጎት እጅግ ከፍተኛ እንደሚሆን ይታወቃል።
አሁን ያለው እና ከ90 በመቶ በላይ የሚሆነውን የሀገራችንን ገቢ እና ወጪ ንግድ ፍሰት የሚያስተናግደው በአንድ ወደብ ላይ ብቻ የተንጠለጠለ የሎጂስቲክስ አቅም የወደፊቱን የሀገራዊ ፍላጎት ማዕበል መሸከም አይችልም።
የሀገራችን የንግድ ልውውጥ መጠን ከሕዝብ ቁጥሩ ጋር ተመጣጣኝ በሆነ መልኩ እያደገ ሲመጣ፣ በአንድ መስመር ላይ የሚኖረው የትራፊክ እና የሎጂስቲክስ ጫና የወጪ ንግድ ወጪን በማናር ሀገራችንን ከዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነት ያወጣታል።
በመሆኑም፣ መጪው የሥነ ሕዝብ ጫና የሎጂስቲክስ አቅም ማስፋፋትን የሚጠይቅ መሆኑ ግልጽ ነው።
በሌላ በኩል፣ ይህ የባሕር በር ፍላጎት በዓለም አቀፍ ሕግጋት ጭምር የተደገፈ የመብት ጥያቄ ነው።
ባሕር በር አልባ ሀገራት በተባበሩት መንግሥታት የባሕር ሕግ ኮንቬንሽን ድንጋጌዎች መሠረት ወደ ባሕር የመድረስ እና የመተላለፍ መብት አላቸው።
የኢንዱስትሪ ሽግግር እያደረገች ላለች ባለ 130 ሚሊዮን ሕዝብ ሀገር ሰፊ የንግድ ፍሰቷን እና የሎጂስቲክስ ሕልውናዋን በሌሎች ሀገራት በጎ ፈቃድ ብቻ ላይ መመርኮዝ ከፍተኛ የኢኮኖሚ እና የደኅንነት ስጋት ነው።
ስለዚህም ይህን ሕጋዊ የመተላለፊያ መብት፣ ወደ ዘላቂ እና የማይናወጥ የጋራ ተጠቃሚነት ወይም የባለቤትነት መብት ማሸጋገር፣ ምክንያታዊ እና ሕጋዊ እርምጃ ነው።
የኢትዮጵያ የባሕር በር እጦት ካልተቀረፈ ግን የሚያመጣው ተጽዕኖ ዘርፈ ብዙ ነው። ከፍተኛ የሎጂስቲክስ ወጪ የሀገር ውስጥ አምራቾችን በዓለም ገበያ ተፎካካሪ እንዳይሆኑ ከማድረጉም ባሻገር፣ በብዙ ሚሊዮኖች ለሚቆጠረው ወጣት ኃይል የሥራ ዕድል የመፍጠር አቅምን ያዳክማል።
በጥቅሉ ሲታይ የኢትዮጵያ የባሕር በር ጥያቄ የቅንጦት ምኞት ወይንም ጂኦ-ፖለቲካዊ የመስፋፋት ፍላጎት አይደለም። ይልቁንም በመጪዎቹ 20 ዓመታት ከ150 ሚሊዮን ለሚሻገረው ሕዝብ አስተማማኝ የምግብ፣ የኃይል፣ የኢንዱስትሪ እና የንግድ አቅርቦትን ለማረጋገጥ የቀረበ የሥነ-ሕዝብ ሕልውና ጥያቄ ነው።
የነገዋ ኢትዮጵያ ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ዕጣ ፈንታ በከፍተኛ ደረጃ የሚወሰነው ዛሬ በሚዘረጋው አስተማማኝ የሎጂስቲክስ፣ የንግድ ሕግጋት እና የባሕር በር ትስስር ላይ በመሆኑ፣ ይህ ጥያቄ የሀገርን ኢኮኖሚያዊ ደህንነት እና የቀጣዩን ትውልድ የመኖር መብት የማረጋገጥ ታሪካዊ ግዴታ ነው።
በበረከት ሽመልስ
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: