Search

ወቅታዊ መልዕክት ለመላ ኢትዮጵያውያን - ከኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን

ዓርብ ነሐሴ 08, 2018 164

በሀገራችን ኢትዮጵያ አዲስ ታሪክና ባህል ሆኖ እየተከናወነ ያለው የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ጉባኤ መካሄድ ከጀመረ እነሆ ዛሬ ነሐሴ 8/2018 . አንድ ወር አስቆጠረ።

ሂደቱ በሀገራችን ሲከናወን ለመጀመሪያ ጊዜ እንደመሆኑ፣ ለምክክር የቀረቡ አጀንዳዎች እጅግ መሰረታዊና ሀገራዊ ፋይዳቸው የጎላ እንደመሆናቸው እንዲሁም የሀገራችንን ብዙኃነት መሰረት ያደረጉ ፍላጎቶች በርካታ ከመሆናቸው ጋር ተያይዞ ጉባኤው የብዙዎች መነጋጋሪያ መሆኑ ለኮሚሽኑ አስገራሚ ነገር ሆኖ አልተገኘም።

በዚህ ሂደት ኢትዮጵያዊያን የጋራ በሚያደርጓቸው ጉዳዮቻቸው ላይ ለመምከር ያሳዩት ቁርጠኝነት፣ በምክክሩ ሂደት እያሳዩት ያለው መከባበር፣ መደማመጥ እንዲሁም እያካበቱት ያለው ማህበራዊ ግንኙነት እጅጉን አመርቂ እና ተስፋ ሰጪም ነው።

ይህ በሀገራችን አዲስ የሆነው የምክክር መድረክ ብዙዎች እንዲተዋወቁ፣የአንተ ችግር የእኔ ነውእንዲባባሉ፣ ለነገ ሀገራቸው የሚጠቅም የጋራ ሃሳብ በመግባባት እንዲያፈልቁ እያስቻለ ይገኛል።

ሂደቱ በኮሚሽኑ የአሰራር ሥነ-ዘዴ መሰረት አንዱን ምዕራፍ እየጨረሰ ወደ ሌላው ምዕራፍ ሲሸጋገር ቆይቶ አሁን ላይ ወደ ወሳኙ ምዕራፍ ላይ ደርሷል።

በኮሚሽኑ ግምገማ መሰረት ያለፈው አንድ ወር የምክክር ሂደት ስኬታማ ሥራዎች የተሰሩበት፣ ምክክር ባህል እንዲሆን መሰረት የሚጥሉ አዳዲስ ጉዳዮች የታዩበት ነው።

ይህ ማለት ግን ሂደቱ ሙሉ በሙሉ  አልጋ በአልጋ ነበረ ማለት አይደለም።  አለመግባባት የሚመስሉ ነገሮች ተስተውለዋል። እነዚህ ነገሮች አለመግባባት አለ ብለን ለተቀመጥን ወገኖች እንግዳ መሆን እንደሌለባቸው የኮሚሽኑ እምነት ነው።

ኮሚሽኑ ካለው አሰራርና ልምድ በመነሳት እንደዚህ ዓይነት ነገሮች ሊያግጥሙ እንደሚችሉ ምክክሩን ከማስጀመሩ በፊት በውል የተረዳው ጉዳይ ነው።ጉዳዩ እንግዳ የመሰለው ለተመካካሪዎችና ወክለው ለመጡት አካል ነው።

ይህ በእንዲህ እያለ በዚህ ስጋት ላይ ኃላፊነት የማይሰማቸው ግለሰቦች እና ቡድኖች እንዲሁም የሚዲያ ባለሙያዎች የሚያሰራጩት ሀሰተኛ መረጃ ሲጨመርበት ደግሞ ነገሩን ምን ያክል ውስብስብ እንደሚያደርገው ኮሚሽኑ ይረዳል።

ለዚህ ነበር ኮሚሽኑ ህብረተሰቡን በኮሚሽኑ ከሚወጡ መረጃዎች እንዲሁም በስፍራው የሚገኙ መገናኛ ብዙኃን ከሚያወጡት መረጃ ውጪ ካሉ መረጃዎች ራሱን በማቀብ ከሀሰተኛ መረጃዎች እንዲጠበቅ ሲያሳስብ የቆየው።

አሁንም ምክክሩ ወደ ወሳኝ ምዕራፍ እየተሸጋገረ መሆኑን ተከትሎ የተዛቡ መረጃዎች በስፋት መውጣታቸውን ስለሚቀጥሉ በድጋሚ መላው ኢትዮጵያዊያን ኮሚሽኑ ከሚያወጣቸው መረጃዎች እንዲሁም በስፍራው የሚገኙ መገናኛ ብዙኃን ከሚያወጡት መረጃ ውጪ ያሉ መረጃዎችን ባለመከታተል ራሱን ከሀሰተኛ መረጃ እንዲጠብቅ ኮሚሽኑ በድጋሚ ያሳስባል።

በዚህ አጋጣሚ የሚዲያ ባለሙያዎች እና ተፅዕኖ ፈጣሪ ግለሰቦችም ጫፍ ያልደረሰ መረጃ በማጋራት በህዝብ ላይ ያልተገባ ብዥታና መደናገርን ከመፍጠር እንድትቆጠቡ ኮሚሽኑ በጥብቅ ያሳስባል።

መሰል ተግባራትን ኮሚሽኑ ለሚመለከተው አካል በማሳወቅ ሙያዊና ሥነ-ምግባራዊ ጥሰት እየፈፀሙ ያሉ የሚዲያ ተቋማትና ባለሙያዎችን ተጠያቂ የማድረግ ስራ እየሰራ መሆኑንም ማሳወቅ ይወዳል። ይህ ክትትልና እርምጃ ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም ማሳሰብ ይወዳል።

ሀገራዊ ምክክር ለሀገራዊ መግባባት!

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: