የኢትዮጵያ የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ትግበራ እና የሙስና ቁጥጥር አዎንታዊና ቀጥተኛ ቁርኝት አላቸው።
አሠራሮችን ከሰው ንክኪ ነጻ በማድረግ እና በዲጂታል ቴክኖሎጂ በመተካት ቢሮክራሲያዊ አሠራርን ግልጽ፣ ተጠያቂነት ያለው እና ፈጣን ማድረግ ያስችላል።
በአገልግሎት መስጫ ቦታዎች የሚፈጠሩ እንግልቶች እና ለሙስና የተጋለጡ ያልተገቡ አሠራሮች በዘመኑ የቴክኖሎጂ ውጤቶች ይጠረጋሉ።
በዚህም የኢትዮጵያ የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ጉዞ አገልግሎት አሰጣጥን በማዘመን ሙስናን የመከላከል አቅምን በከፍተኛ ደረጃ ያሳድጋል።
ለአብነትም በአገልግሎቱ የሰው ንክኪን በመቀነስ የመንጃ ፈቃድ፣ ፓስፖርት፣ የንግድ ፈቃድ እና መሰል አገልግሎቶች በኦንላይን መሰጠታቸው ከአገልጋይ እና ተገልጋይ ቀጥታ ንክኪ ጋር ተያይዘው የሚጠየቁ የጉቦ አጋጣሚዎችን መቀነስ ያስችላል።
እንደ ቴሌብር ያሉ የክፍያ ሥርዓቶች፣ የባንክ አፕሊኬሽኖች እና የመንግሥት የክፍያ ሥርዓቶች (ለምሳሌ የትራፊክ ቅጣት፣ ታክስ እና ሌሎች የአገልግሎት ክፍያዎች) በጥሬ ገንዘብ አለመፈጸማቸው የፋይናንስ እንቅስቃሴው እንዲመዘገብ በማድረግ ሕገ ወጥ የገንዘብ ዝውውርን በማገድ እና የታክስ ስወራን በማስቀረት ሙስናን ይገታሉ።
በሌላ በኩል የዲጂታል ኢትዮጵያ ትግበራ ውጤት የሆነው የፋይዳ ዲጂታል መታወቂያ የባዮሜትሪክስ መረጃን በመጠቀሙ፣ የሐሰት መታወቂያ ማዘጋጀት እንዲሁም ሰዎች በሌሉበት ስማቸውን በመዝገብ በማስፈር የሚፈጸምን የሦስተኛ ወገን አላግባብ ተጠቃሚነት ያስቀራል።
ዘርፉ የጨረታ ሒደቶች በዲጂታል መድረክ እንዲከወኑ ማስቻሉ መረጃዎችን የመደበቅ እና የመመሳጠር ዕድሎችን በማስቀረት ለሁሉም ተወዳዳሪዎች እኩል ዕድል ይፈጥራል።
የሒሳብ መዝገቦች እና የውሳኔ አሰጣጥ ሒደቶች በዲጂታል መንገድ ሲቀመጡ የቁጥጥር አካላት ያልተለመዱ አሠራሮችን በቀላሉ እና ፈጥነው እንዲለዩ ያስችላቸዋል።
በጥቅሉ ኢትዮጵያ የጀመረችው የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ጉዞ በተጠቀሱት እና በሌሎች ትግበራዎች ሙስናን መውጊያ መሣሪያ ሆኖ ያገለግላል፤ በዘመናዊ ቴክኖሎጂ የሙስና ዕጣ ውድቀት እና ውድቀት ብቻ ይሆናል።
በዓይናለም ሃድራ
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: