Search

ከጥሬ ሀብት ወደ እሴት ጭማሪ፡ የኢትዮጵያ ማዕድን ዘርፍ አዲሱ ምዕራፍ

ማክሰኞ ነሐሴ 12, 2018 176

ኢትዮጵያ በተፈጥሮ ሀብት የበለፀገ የምድር ገፅ ውበት ብቻ ሳይሆን፣ ከምድር በታች የተሸሸገ ታላቅ የኢኮኖሚ አቅም ባለቤት ናት።

ለረጅም ዘመናት አቅሙ በሚገባ ሳይወጣ የቆየው የማዕድን ዘርፍ፣ በአሁኑ ወቅት የኢኮኖሚ መዋቅርን በመቀየር፣ የውጭ ምንዛሬ ግኝትን በማሳደግ እና ለዜጎች ሰፊ የሥራ ዕድል በመፍጠር ረገድ የነገዋ ኢትዮጵያ አዲስ ተስፋ ሆኖ ብቅ ብሏል።

በተለያዩ አካባቢዎች የሚገኙት የወርቅ፣ የሊቲየም፣ የፖታሽ፣ የታንታለም፣ የከሰል ድንጋይ እና የከበሩ ድንጋዮች ክምችት ኢትዮጵያን በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ የማድረግ ከፍተኛ አቅም አላቸው።

በተለይም ለዘመናዊ የቴክኖሎጂ ውጤቶች እና ለኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች ባትሪ ምርት እጅግ ተፈላጊ የሆነው የሊቲየም ማዕድን፣ እንዲሁም በአፋር ዳሎል አካባቢ በከፍተኛ መጠን የሚገኘው እና ለግብርናው ዘርፍ ወሳኝ የሆነው የፖታሽ ክምችት የዓለም አቀፍ ኢንቨስትመንት ሳቢ መዳረሻ እያደረጓት ነው።

ከዚህ በተጨማሪም በደቡብ እና ኦሮሚያ ክልሎች የሚገኘው የታንታለም ክምችት ለዓለም አቀፍ የኤሌክትሮኒክስ ኢንዱስትሪ ትልቅ ግብዓት በመሆን ኢኮኖሚያዊ ፋይዳውን እያጎላው ይገኛል።

የማዕድን ዘርፉን ዘመናዊ እና ቀልጣፋ ለማድረግ በተወሰዱ የፖሊሲ ማሻሻያዎች፣ የሕገ-ወጥ ማዕድን ዝውውርን ለመግታት በተደረጉ ጥረቶች እና ለሀገር ውስጥ እንዲሁም ለውጭ ባለሀብቶች በተፈጠሩ ሰፊ የኢንቨስትመንት ዕድሎች ዘርፉ አዲስ ሕይወት ዘርቷል።

ከዚሁ ጎን ለጎን ሚሊዮን ዜጎች የተሰማሩበትን የባህላዊ ማዕድን አውጪዎች አደረጃጀት ማዘመን፣ የፋይናንስ እና ቴክኖሎጂ አቅርቦት ማመቻቸት እንዲሁም የአካባቢ ጥበቃን ያማከለ አሠራር መዘርጋቱ ተወዳዳሪነትን እና ፍትሐዊ ተጠቃሚነትን አረጋግጧል።

ማዕድናትን በጥሬው ወደ ውጭ ከመላክ ይልቅ በሀገር ውስጥ እሴት ጨምሮ ለዓለም አቀፍ ገበያ ማቅረብ ላይ የተጣለው ትኩረት ለኢንዱስትሪ ሽግግሩ ታላቅ መሠረት እየጣለ ነው።

ይህንንም ተከትሎ ተግባራዊ እየተደረጉ ያሉ የማዕድን ማቀነባበሪያ ፋብሪካዎች ግንባታ ከተጨማሪ የውጭ ምንዛሬ ባሻገር የቴክኖሎጂ ሽግግርን፣ የሥራ ዕድል ፈጠራን እና የሙያ ክህሎትን በከፍተኛ ደረጃ ያጎለብታሉ።

በመሆኑም የምድር ስር ሀብታችን ብልፅግናን ለማፋጠን እና ለትውልድ የሚሻገር ዘላቂ ኢኮኖሚ ለመገንባት የተጣለ የኢትዮጵያ አዲስ የእድገት ምሰሶ ነው።

በሔዋን ጌታቸው

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: