Search

'ጽምዶ' በግብፅና ሻዕቢያ መሪነት የሚዘወር ጽንፈኛ ኃይሎች የጥፋት ስብስብ ነው - ሌተናል ጀኔራል ዮሐንስ ገብረ መስቀል

ማክሰኞ ነሐሴ 12, 2018 136

'ጽምዶ' በግብፅና ሻዕቢያ መሪነት የሚዘወር ስትራቴጂክ አጋርነት የሌላቸው በአየር ላይ የተበተነ የአጥፍቶ ጠፊ ጽንፈኛ ኃይሎች ስብስብ መሆኑን የቀድሞው ወታደራዊ አመራር ሌተናል ጀኔራል ዮሐንስ ገብረ መስቀል ገለጹ።

የቀድሞው ወታደራዊ አመራር ሌተናል ጄኔራል ዮሐንስ ገብረመስቀል እንዳሉት፤ በግብፅ፣ ሱዳንና በሻዕቢያ መሪነት የሕገ-ወጡ ሕወሓት፣ በኦሮሚያና አማራ ክልል የሚንቀሳቀሱ ጽንፈኛ ኃይሎች ጥምረት የአጥፍቶ ጠፊ ስብስብ ነው።

'ጽምዶ' በሚል ስያሜ ጥምረት በመፍጠር በሕዝብ ስም ሲምሉና ሲገዘቱ የሚውሉ ፀረ-ኢትዮጵያ ኃይሎችም በሥልጣን ጥማት የሰከሩና እርስ በእርሳቸው የማይተማመኑ የጥፋት ኃይሎች መሆናቸውን ገልጸዋል።

ጥምረቱም የኢትዮጵያን ታሪካዊ ጠላቶች የሀገርን ዕድገትና ብልጽግና ጉዞ የማዳከም ዓላማ በማንገብ የሚንቀሳቀሱ ፀረ-ሕዝብ ኃይሎች የወጠኑት መሆኑን ተናግረዋል።

የሻዕቢያ ኃይል ከጥፋት ውጪ የልማትና ዕድገት ትብብር አይታየውም ያሉት ሌተናል ጄኔራል ዮሐንስ፤ ኤርትራንም የልማት ሽታ የማይውቃት የስደት፣ ሞትና እንግልት ምድር አድርጓት መቀጠሉን አንስተዋል።

የሕገ-ወጡ ሕወሓትን፣ የኦሮሚያና አማራ ክልል ጽንፈኛ ኃይሎችን 'ጽምዶ' በሚል ስያሜ ያለ አንዳች ስትራቴጂካዊ አጋርነት ለጥፋት ዓላማው ማስፈጸሚያነት በማጣመር ድጋፍ እያደረገ መሆኑን ጠቅሰዋል።

'ጽምዶ' ጥምረትም ተስፋ መቁረጥ የወለደው ያለአቻ ጋብቻ የጥፋት እንቅስቃሴ መሆኑን አብራርተዋል።

'ጽምዶ' ጥምረትም በሻዕቢያ የበላይ ጠባቂ ኢሳያስ አፈወርቂ ቀጭን ትዕዛዝ የሚመራና በራሱ የመወሰን አቅም የሌለው፣ የኢትዮጵያና ሕዝቦቿ ታሪካዊ ጠላቶች ዓላማ አስፈጻሚ ነው ብለዋል።

የጥፋት ጥምረቱ በታሪካዊ ጠላቶች በሚሰፈርለት ቀለብ ልክ የሚያሰራጨው ስሁት ፕሮፓጋንዳም ሕዝብን በማወናበድ ላይ የተመሠረተ መሠረተ ቢስ ስብስብ መሆኑን በተግባር እንደሚያመላክት ገልጸዋል።

ሕገ-ወጡ የሕወሓት ቡድን በጥፋት ጥምረቱ 'ጽምዶ' ስብስብ የፈጠረው ያልተቀደሰ ጋብቻም ከጥፋት አጋሩ ሻቢያ የቀሰመው የአጥፍቶ ጠፊነት ባህሪ መሆኑን አንስተዋል።

የትግራይ ሕዝብ በክልሉ በቅሎ ከጎለመሰው ሕገ-ወጡ የሕወሓት ስብስብ በተጨማሪ ሻዕቢያ ቁጥር አንድ መሆኑም አስገንዝበዋል።

በዚህም የትግራይ ህዝብ የጀመረው የሕገ-ወጡ ሕወሓት ፀረ-ትግል በማፋፋም ከጫንቃው ላይ በማውረድ ሰላምና ልማትን ማፋጠን እንደሚኖርበት አስረድተዋል።

በትጥቅ ትግል ታግዞ የሚካሄድ ኋላቀር የጠብመንጃ እንቅስቃሴ ሀገርና ሕዝብን ከማጎሳቆል የዘለለ አንዳች ፋይዳ እንደሌለው ማስረዳታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: