ከተቆረቆረች ረጅም ዓመታትን ያስቆጠረችው የሶማሌ ክልሏ ዋና ከተማ - ጂግጂጋ፤ የንግድና የባህል ማዕከልነቷ ጎልቶ ቢነገርም፣ ከዘመኑ ቴክኖሎጂና ዘመናዊነት ጋር ተራርቃ ሰንብታለች።
አሁን ግን የምስራቋ ፈርጥ- ጂግጂጋ- ዘመን መጥቶላት የዕድሜዋን ያህል ዘመናዊነትን የሚያላብሷት በርካታ የኮሪደር እና የከተማ ውበት ፕሮጀክቶችን በማካሄድ ላይ ትገኛለች።
በከተማዋ የኮሪደር ልማት የ16ቱ ፕሮጀክቶች በመሃል ከተማ በአራቱም አቅጣጫዎች፡- የሳይክል እና የእግረኛ መንገዶች እና ሰባት ውበትን የተጎናፀፉ ፋውንቴኖች ተገንብተዋል። በለውጡ ሂደትም የአካባቢው ማህበረሰብ ተሳትፎ እና አስተዋጽኦ ከፍተኛ ነው፡፡
በሌላ በኩል የሸበሌ ሪዞርት የሶማሌን ባህል የሚያስተዋውቁ ምግብ ቤቶች የባህል ማዕከል እና አዳራሾችን በማቀፍ የቱሪዝም መዳረሻ አድርጓታል።
ሀረር ኬላ ደግሞ ለአካባቢው ትልቅ የቱሪዝም እና የኢኮኖሚ ሀብት የሚሆን ዘመናዊ ፓርክ ነው። ፓርኩ የመኪና ማቆሚያ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች ቻርጅ ማድረጊያ፣ የተሽከርካሪ ማቆሚያ፣ የልጆች መጫወቻ ስፍራዎች፣ አምፊ ቴአትር፣ የቅርጫት ኳስ፣ የእጅ ኳስ እና የሜዳ ኳስ መጫወቻዎችን ይዟል።
ጉድዋል ፓርክ፣ ለነዋሪዎች ተጨማሪ የመዝናኛ ስፍራ ከመፍጠር ባለፈ በከተማዋ የሕዝብ ቦታዎችን በማስፋፋት የከተማ ኑሮን የበለጠ ምቹና ማራኪ ለማድረግ አግዟል።
ይህ የንግድና አገልግሎት ዘርፍ መነቃቃት፣ የተስፋፉ መንገዶችና የጎዳና ላይ መብራቶች ለምሽት ኢኮኖሚ መንገድ በመክፈታቸው የሆቴሎች፣ የሬስቶራንቶችና የመዝናኛ ቦታዎች ገቢ እንዲያድግ አስተዋፅኦ ያበረክታል።
የጂግጂጋን የቆየ ታሪካዊና ባህላዊ አሻራ ሳይሸርፍ የተከናወነው የኮሪደር ልማት፣ የሀገር ውስጥና የውጭ ሀገር ጎብኚዎች በሰላምና በምቾት ከተማዋን እንዲጎበኙ ምቹ ሁኔታን ፈጥሯል።
የቱሪስቶች ፍሰት መጨመር በአቀባበል፣ በትራንስፖርት፣ በባህላዊ ቁሳቁሶች ሽያጭ እና በአነስተኛና መካከለኛ ንግዶች ላይ ለበርካታ ነዋሪዎች የሥራ ዕድል የሚፈጥር ነው።
ዘመናዊው የከተማ ገጽታ ለቱሪዝም መሠረተ ልማት የሚወጡ ኢንቨስትመንቶችን በመሳብም የከተማዋን አጠቃላይ የገቢ ምንጭ አሳድጎታል።
እነዚህ ፕሮጀክቶች ከተማይቱን ከንግድ መዓከልነት በተጨማሪ ወደ ቱሪዝም ማዕከልነት ያሸጋገሩ ሆነዋል።
በልዩ እሸቱ
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: