Search

የባሕር በር እና የፕሮፌሰር ሪቻርድ ፓንክረስት ሕያው ምስክርነት

ረቡዕ ነሐሴ 13, 2018 208

የኢትዮጵያ የቀይ ባሕር ባለቤትነት እና የባሕር በር ጉዳይ በዓለም አቀፍ የታሪክ ድርሳናት፣ በጥንታዊ የሥልጣኔ ቅርሶች፣ እንዲሁም በታላላቅ የውጭ ሀገር ታሪክ ምሁራን ጥልቅ ምርምር የተረጋገጠ፣ የማያወላዳ ፍጹም ታሪካዊ ሐቅ ነው።

የኢትዮጵያ ታሪክ ከቀይ ባሕር ማዕበል፣ ከሕንድ ውቅያኖስ የንግድ መስመር፣ እንዲሁም ከዓለም አቀፍ የጂኦ-ፖለቲካዊ መስተጋብር ጋር እጅግ የተቆራኘ ነው።

ይህንን ሐቅ ፈልፍሎ በማውጣት እና ለዓለም በማሳየት ረገድ ደግሞ፣ የኢትዮጵያ እውነተኛ ወዳጅ፣ በልባቸው ሙሉ ኢትዮጵያዊ የሆኑት ታላቁ ምሁር ፕሮፌሰር ሪቻርድ ፓንክረስት የማይተካ ሚና ተጫውተዋል።

ሐቅ ነው፣ ፕሮፌሰር ፓንክረስት ለኢትዮጵያ ያላቸው ፍቅር ወደር የለውም፤ ስለ ኢትዮጵያ የባሕር ታሪክ የጻፉት ግን ከስሜት በመነጨ ወገንተኝነት ሳይሆን፣ " ኢትዮጵያን ቦርደርላንድስ" በተሰኘው መጽሐፋቸው እና በሌሎችም በርካታ ጥናቶቻቸው ባቀረቧቸው በማስረጃ የተደገፉ ምሁራዊ እና የማይካዱ እውነታዎች ላይ ተመሥርተው ነው።

እኚህ ዕውቅ ምሁር ባደረጓቸው ጥናቶች መሠረት፣ የኢትዮጵያ የባሕር በር ባለቤትነት በሚከተሉት ታሪካዊ ዘመናት በጉልህ ይታያል፦

የኢትዮጵያ የባሕር ኃያልነት ገና ከጥንታዊቷ ፑንት ዘመን ይጀምራል።

ኢትዮጵያ በጥንታዊ ስሟ "ፑንት" እየተባለች በምትጠራበት ጊዜ (3407 እስከ 2888 . ጀምሮ) በቀይ ባሕር ላይ ፍጹም የሆነ የንግድ እና የጂኦ-ፖለቲካ የበላይነት ነበራት።

ግብጻውያን ነገሥታት፣ በተለይም እንደ ንጉሥ ሳሁር እና ንግሥት ሐትሸፐስት ያሉት ኃያላን መሪዎች፣ በሺዎች የሚቆጠር ስልቻ ከርቤ፣ የተመረጠ ዕጣን፣ የዝሆን ጥርስ እና ውድ ወርቅ ለመውሰድ መርከቦቻቸውን ወደ ኢትዮጵያ ዳርቻዎች በተደጋጋሚ ይሰዱ ነበር።

በተጨማሪም የንጉሥ ሰለሞን መርከቦች ልዩ ልዩ ማዕድናትን እና የከርቤ ዛፎችን ለመፈለግ ወደ አፋር ጠረፎች ይመጡ እንደነበር ፕሮፌሰሩ በታሪክ መዛግብት አስደግፈው ያስረዱናል።

ወደ መካከለኛው ዘመን ስንመጣም፣ የኢትዮጵያ የባሕር ላይ ንግድ እና የፖለቲካ ተሳትፎ ፈጽሞ አልተቋረጠም።

ሙስሊሞች ቀይ ባሕርን በተቆጣጠሩበትና እስልምና በስፋት በተሰራጨበት በዚያ ዘመንም ቢሆን፣ ኢትዮጵያውያን ነገሥታት የባሕር በሮቻቸውን በንቃት ይጠቀሙ ነበር።

ለአብነት ያህል፣ አፄ ልብነ ድንግል ወርቅና የዝሆን ጥርስን ጨምሮ ልዩ ልዩ ምርቶችን በሰፊው ወደ ዓረብ ሀገር ይልኩ ነበር። ከአዳል ሡልጣኔት አሚር ማሕፉዝ ጀምሮ እስከ አሕመድ ግራኝ (1506-1543) ዘመን ድረስ ያሉት መሪዎች፣ ዘይላና በርበራ የተባሉትን ቁልፍ የባሕር በሮች በመጠቀም የሩቅ ምሥራቅንና የመካከለኛው ምሥራቅን ንግድ ከኢትዮጵያ ጋር በከፍተኛ ደረጃ ያስተሳስሩ ነበር።

የኢትዮጵያ የባሕር ላይ ታሪክ በቀይ ባሕር ጠረፍ ላይ ብቻ የተወሰነም አልነበረም።

ፕሮፌሰር ፓንክረስት 1965 .. ባሳተሙት ጥልቅ ጥናት እንዳስረገጡት፣ የኢትዮጵያ የባሕር ንግድ አድማሱን አስፍቶ በሕንድ ውቅያኖስ ዳርቻዎች በዘይላ፣ በበርበራ፣ በኪስማዮ፣ በሞቃዲሹ እና አልፎም እስከ ዛንዚባር ድረስ ይዘረጋል።

በዚያን ጊዜ በሐረር በኩል ብቻ በዓመት 15 ሚሊዮን እስከ 22.5 ሚሊዮን ኪሎ ቡና እና ቢያንስ አንድ ሚሊዮን ኪሎ የዝሆን ጥርስ በእነዚህ ወደቦች አማካኝነት ወደ ውጭ ገበያ ይላክ እንደነበር መዛግብት በግልጽ ያሳያሉ።

ከዚህም ባሻገር፣ ፕሮፌሰሩ የባንያውያን (ሕንዳውያን) ነጋዴዎችን ሰፊ ተሳትፎ በምጽዋና በዳህላክ ደሴቶች ላይ አጥንተዋል። እነዚህ ነጋዴዎች በንግድ መርከቦቻቸው ተራ ብረት፣ ዓረብ ብረት፣ እና "ሞቻ" የሚባል የሕንድ ልብስ እያመጡ ከአዱሊስ እስከ ዘይላ ድረስ ገብተው ከኢትዮጵያውያን ጋር ከፍተኛ የሆነ የንግድ ልውውጥ ሲያካሂዱ ቆይተዋል።

 

በቅርቡ በደብረ ዳሞ በተደረገው የአርኪዮሎጂ ቁፋሮ የተገኙት የብራህማን ቋንቋ የተጻፈባቸው ቀለበቶችና የወርቅ ሳንቲሞች የዚህ የውቅያኖስ አቋራጭ ንግድ ሕያው ማስረጃዎች ናቸው።

እነዚህ የፕሮፌሰር ሪቻርድ ፓንክረስት ሳይታክቱ የቆፈሯቸው ምሁራዊ እውነታዎች አንድ ትልቅ ቁም ነገር ይነግሩናል፤ ኢትዮጵያ የባሕር በር ባለቤትነት ታሪኳን የተነጠቀችው በቅርብ ጊዜ በተሸረበ የፖለቲካ ሴራ እንጂ በተፈጥሮ አለመሆኑን።

ዛሬ ላይ ዘመኑን የዋጀው አዲሱ የኢትዮጵያ ትውልድ ይህንን ታሪካዊ ሐቅ በሚገባ ተገንዝቧል። የኢትዮጵያ ሕዝብ ከተኛበት የዝምታ እንቅልፍ ነቅቷል፤ ታሪካዊ፣ ሕጋዊና ተፈጥሯዊ መብቱን ለማስመለስም ቁርጠኛ ሆኖ ተነስቷል።

ፕሮፌሰር ፓንክረስት፣ እንደ አንድ የኢትዮጵያ ውድ ልጅ፣ በምሁራዊ ብዕራቸው ለዓለም ያሳወቁትና ያቆዩልን የታሪክ ዐደራ ከንቱ ሆኖ አይቀርም!

ኢትዮጵያ የዚህን የነቃ ትውልድ አቅም ተጠቅማ፣ በማንም ላይ ጉዳት ሳታደርስ፣ በፍትሕና በጋራ ተጠቃሚነት መርሕ ወደ ተፈጥሯዊ የባሕር በሯ መመለሷና ዳግም የባሕር ባለቤት መሆኗ የማይቀር ታሪካዊ እውነት ነው!

የትውልዱ መነሳት ተስፋ የሰነቀ ነው፤ ታላቋ ኢትዮጵያም ወደ ቀደመ የጂኦ-ፖለቲካዊ ልዕልናዋና የባሕር ዳርቻዋ በክብር ትመለሳለች!

በአዶኒያስ ወልደአረጋይ

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: