ወይዘሮ ኬርያ ኢብራሂም ከኢቲቪ ትግርኛ ጋር ባደረጉት ቃለ መጠይቅ፣ በህገ ወጡ ህወሓት ድርጅታዊ ውድቀት፣ በህዝብ ላይ እየደረሰ ባለው መከራ እና በወደፊት የትግራይ ተስፋ ዙሪያ ነጥቦችን አንስተዋል።
ወይዘሮ ኬርያ እንደገለጹት፣ ህገ ወጡ ህወሓት አሁን ከመስመሩ ወጥቶ ከላይ እስከ ታች ባለው መዋቅሩ በሙስና፣ በስልጣን ጥም፣ በግላዊ ጥቅም እና በውስጥ ክፍፍል ሳቢያ ወደ ፈጣን መበስበስና መበታተን አምርቷል።
ድርጅቱ ህዝባዊ ወገንተኝነቱን አጥቶ ስልጣንን ለግል ፍላጎት ማሳኪያ በማድረጉ፣ በ60ዎቹና በ70ዎቹ የነበረውን አደገኛ ልዩነትና ክፍፍል ወደ አዲስ ጦርነት በመቀየር ላይ ይገኛል።
ይህ ዓይነቱ አካሄድ፣ በኃይልና በፍርሃት ሰዎችን የማስፈራራት አካሄድ (የፌስቡክ ፖለቲካን ጨምሮ) እና ከሻዕቢያ ጋር አደገኛ ጥምረት በመፍጠር የተካሄደው ሴራ፣ የትግራይን ህዝብ ለተጨማሪ ዋጋና ለመጨረሻ ጥፋት የሚዳርግ፣ የጠለቀ ንቅናቄና ግልጽ ባንዳነትን የሚያሳይ ነው።
በጦርነቱ ምክንያት በተለይም ሴቶችና ህፃናት ገደብ የለሽ ግፍ፣ እንግልትና ስቃይ አስተናግደዋል። ህዝቡ መብቱ ተገፎና እንደ ንብረት ተቆጥሮ ለግል ጥቅም ሲባል ለጦርነት ሲማገድ መኖሩ የቡድኑን ጥልቅ ንቀት ያሳያል።
ስለሆነም አሁን ያለው ትውልድ በቃ ሊል እንደሚገባና የትግራይ ህልውና ከእንግዲህ በልጆቿ ደም መፋሰስ ሳይሆን፣ በህግ የበላይነት፣ በብልህ ሀሳብ፣ በዕውቀት፣ በኢንጂነሪንግ፣ በህክምና፣ በፋብሪካዎችና በሳይንሳዊ እድገት ብቻ መረጋገጥ እንዳለበት አፅንኦት ሰጥተዋል።
ወይዘሮ ኬርያ ሁሉም ወገን ለሰላም ቅድሚያ በመስጠት፣ ቂም በቀልን አስወግዶ፣ በክብ ጠረንጴዛ ውይይትና በበሰለ ሀሳብ ልዩነቶችን መፍታት እንዳለበት ጥሪ አቅርበዋል።
በአብርሃም አስኳሉ
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: