Search

ወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ በሳይበር ደህንነት ዙሪያ የሰለጠኑ ወጣቶችን አስመረቀ

ረቡዕ ነሐሴ 13, 2018 212

የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር (ኢመደአ) ከወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር በክረምት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት መርሃ-ግብር 5 ዙር በሳይበር ደህንነት ዙሪያ ሲያሰለጥናቸው የቆዩ ወጣቶችን አስመርቋል።

በምረቃ ስነ-ስርዓቱ ላይ የተገኙት የኢመደአ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ወይዘሮ አስቴር ዳዊት እንደገለጹት፤ ተቋሙ በየዓመቱ በክረምት ወቅት ከተለያዩ አካባቢዎች ወጣቶችን በመመልመል ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ጋር በመተባበር በሳይበር ደህንነት ዙሪያ ያሰለጥናል።

ወጣቶች ተፈጥሯዊ ክህሎታቸውን በቴክኖሎጂ በማስደገፍ ለዲጂታል ኢትዮጵያ እውን መሆን የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እንዲያበረክቱ እንደሚጠበቅባቸውም አሳስበዋል።

ለዚህም ስኬት ወጣቶች ቴክኖሎጂን እንዲለማመዱ ማድረግ እና በተለይም በታዳጊዎች ላይ በትኩረት መስራት ከፍተኛ ፋይዳ እንዳለው ገልጸዋል።

የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ቢሮ ኃላፊ ቦጋሌ ቦሻ (/) በበኩላቸው፤ የሀገሪቱን የሳይበር ደህንነት ሉዓላዊነትና ዘላቂ ዕድገት ለማረጋገጥ በዘርፉ በስፋት መስራት ወሳኝ መሆኑን ጠቁመዋል። ወጣቱ ትውልድ ለቴክኖሎጂ ዘርፍ ልዩ ትኩረት በመስጠት መንግስት ያመቻቸውን ምቹ አጋጣሚዎች በአግባቡ መጠቀም እንዳለበትም አሳስበዋል።

የወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ ምክትል ፕሬዚዳንት አክበር ጩፋ (/) ዩኒቨርሲቲው ለቴክኖሎጂው ዘርፍ ቅድሚያ በመስጠት የዲጂታል ኢትዮጵያን ራዕይ ለማሳካት የሚደረገውን ሀገራዊ ጉዞ በግንባር ቀደምትነት እየደገፈ እንደሚገኝ አስረድተዋል።

ሰልጣኝ ወጣቶች በሰጡት አስተያየት፤ ያገኙት ስልጠና ሀገሪቱ በቴክኖሎጂው ዘርፍ ለምታከናውናቸው ተግባራት አዎንታዊ አስተዋጽኦ ለማበርከት የሚያስችላቸው ከመሆኑም በላይ የራሳቸውን የፈጠራ አቅም ለማሳደግ እንደሚጠቀሙበት አረጋግጠዋል።

በዚሁ የምረቃ መርሃ-ግብር ላይ የወላይታ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ረዳት ፕሮፌሰር ሳሙኤል ተሰማ፣ የወላይታ ሶዶ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ እታገኝ ኃይለማርያም እና ሌሎች የፌዴራልና የክልል ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።

በትዕግስቱ ቡቼ

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: