በዓለም ታሪክ ውስጥ ታላላቅ ሀገራት ከአስቸጋሪ ፈተናዎች እና ከልዩነት ማዕበል ውስጥ ወጥተው ጠንካራ ሀገረ-መንግሥት መገንባት የቻሉት በውይይት እና በምክክር ነው።
ሀገራችን ኢትዮጵያ ሁሉንም ያቀፈ ሀገራዊ ምክክር ስታካሂድ፣ ይኸው የሰለጠነ እና የረጅም ጊዜ ዕይታ ውጤት የሆነው መንገድ ላይ መሆኗን ያረጋግጣል።
በአዋጅ ቁጥር 1265/2014 የተቋቋመው ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን፣ ይህንን ታሪካዊ ሂደት የብዙዎችን ተስፋ የሰነቀ እንዲሆን እያደረገው ይገኛል። ይሁንና ሂደቱ ላይ በቀጥታ ከመሳተፍ ይልቅ ከውጭ ሆነው የሚሰነዘሩ አላስፈላጊ አሉታዊ አስተያየቶች እና ትችቶች አልጠፉም።
እነዚህ ከውጭ የሚመጡ አሉታዊ ምልከታዎች የኢትዮጵያን የዕርቅ ጉዞ በፍፁም ሊያስተጉሉት አይችሉም።
የአጀንዳ ማሰባሰብ ምዕራፉን በተለያዩ የሀገራችን ክፍሎች ሁሉንም የማኅበረሰብ ከፍል ባሳተፈ መልኩ ያካሄደው የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር መሠረቱ እና ባለቤቱ ራሱ የኢትዮጵያ ሕዝብ መሆኑን በተግባር ያረጋገጠ ናቸው።
ከውጭ የሚሰነዘሩት አሉታዊ ትችቶች የሀገራችንን ውስብስብ ማኅበራዊ እና ታሪካዊ መስተጋብር በጥልቀት ካለመረዳት፣ ወይም ደግሞ ሂደቱ የሚያመጣውን ዘላቂ ሰላም ካለመመኘት የሚመነጩ ናቸው።
እንደነዚህ ያሉ ውጫዊ ድምፆች እና ተስፋ አስቆራጭ ትርክቶች በምክክሩ ጠንካራ መሠረት ላይ የተደቀነ እንቅፋት ሊሆኑ አይችሉም።
ይልቁንም ሕዝባችን የጋራ ቤቱን በጽኑ መሠረት ላይ ለመገንባት ያለውን ቁርጠኝነት እና አንድነት የበለጠ የሚያጠናክሩ ናቸው።
ኢትዮጵያ በታሪኳ የማትበገር እና ፈተናዎችን ሁሉ ወደ መልካም አጋጣሚ የምትቀይር ታላቅ ሀገር ናት።
በምክክር ኮሚሽኑ አማካኝነት እየተከናወኑ ያሉ የዜጎች የምክክር መድረኮች፣ መሰረት ያለው እና የኢትዮጵያውያንን የጋራ እውነት እና ፍላጎት የሚያንፀባርቁ በመሆናቸው ውጤታማነታቸው የታመነ ነው።
ሀገራችን ይህንን ታሪካዊ አጋጣሚ በአግባቡ በመጠቀም በልዩነቶች መካከል ድልድይ በመገንባት እና የጋራ ብሔራዊ መግባባትን በመፍጠር ፀንታ ትቆማለች።
ምክክሩ የዘመናት ቁስሎቻችንን አክሞ፣ የሰላም፣ የፍትሕ እና የእኩልነት ፍሬ እንደሚያፈራ ምንም ጥርጥር የለውም።
የውጭ ትችቶች እና አሉታዊ አስተያየቶች ያልፋሉ፤ የኢትዮጵያ ሕዝብ በውይይትና በምክክር የሚገነባት ጠንካራና የተባበረች ኢትዮጵያ ግን ለትውልድ ፀንታ ትኖራለች።
በሔዋን ጌታቸው
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: