Search

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የጤናውን ዘርፍ ለማሳደግ ታሪካዊ አጋርነቱን አጠናከረ

ሓሙስ ነሐሴ 14, 2018 70

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የኢትዮጵያ የጤና ፌዴሬሽን ከጤና ሚኒስቴር ጋር በመተባበር የሚያዘጋጀውን 13ኛው የምሥራቅ አፍሪካ የጤና እንክብካቤ ፌዴሬሽን (EAHF) ጉባኤ እና ዓለም አቀፍ የጤና ኤግዚቢሽን 2026 ዋና ስፖንሰር በመሆን በይፋ ተሰይሟል።

በአዲስ አበባው አድዋ ድል መታሰቢያ ሙዚየም የሚካሄደውን ይህን ታላቅ አህጉራዊ ጉባኤ ባንኩ በስያሜ ስፖንሰርነት ለመደገፍ የወሰነው፣ ጤናማ ኅብረተሰብ ሳይኖር ዘላቂ የሀገር ኢኮኖሚ ማሳደግ እንደማይቻል በጽኑ በማመኑ ነው።

የዚሁ አጋርነት ማበሰሪያ የጋራ ጋዜጣዊ መግለጫ በዛሬው ዕለት ነሐሴ 14 ቀን 2018 .. በባንኩ አዲስ ዋና መሥሪያ ቤት ሕንጻ የተሰጠ ሲሆን፣ የባንኩ የደንበኞች ኤክስፒሪየንስ ምክትል ፕሬዝዳንት እና የኢትዮጵያ ጤና ፌዴሬሽን አመራሮች በጋራ በመሆን ዝርዝር መረጃዎችን ለሚዲያ አካላት አቅርበዋል።

ባንኩ የምሥራቅ አፍሪካ አገራት በጤናው ዘርፍ ከውጭ እርዳታና ተጽዕኖ ተላቀው የጤና ሉዐላዊነትን እንዲያሰፍኑ አስፈላጊውን የፋይናንስ ድጋፍ ለማመቻቸት ቁርጠኝነቱን አረጋግጧል።

በዚህም መሠረት የሀገር ውስጥ መድኃኒት አምራቾችንና የጤና አገልግሎት ሰጪዎችን በማጠናከር ረገድ የሥራ ማስኬጃ ካፒታል፣ የውጭ ምንዛሬ እና የረጅም ጊዜ ብድር የሚያቀርብ ሲሆን፣ በዲጂታል የፋይናንስ አገልግሎቶቹና በሰፊ የቅርንጫፍ አውታሩ አማካይነት የሕክምና ክፍያዎችንና የጤና መድንን ተደራሽ ለማድረግ ይሠራል።

በተጨማሪም በአፍሪካ ነጻ ንግድ ቀጠና (AfCFTA) ማዕቀፍ የድንበር ተሻጋሪ የጤና ኢንቨስትመንቶችንና የንግድ ፋይናንስን በማጠናከር አህጉራዊ የጤና ዋስትናን በሀገር ውስጥ ካፒታል ለማረጋገጥ ያለመ ነው።

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በጤናው ዘርፍ ለተሰማሩ አምራችና አገልግሎት ሰጪ ድርጅቶች በቢሊዮን የሚገመት የብድርና የውጭ ምንዛሬ አቅርቦት ማድረጉ የሚታወስ ሲሆን፣ በማኅበራዊ ኃላፊነት ዘርፍም በቅርብ ዓመታት ውስጥ ብቻ 481.25 ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ አድርጓል።

ከነዚህም መካከል በዘጠኝ ክልሎች ለተገነቡ የጤና ጣቢያዎች 254.35 ሚሊዮን ብር፣ ለሕፃናት ልብ ሕክምና ማእከል፣ ለኢትዮጵያ ዓቅን ባንክና ለኮቪድ-19 መከላከያ 14.8 ሚሊዮን ብር፣ እንዲሁም ለአረጋውያንና አእምሮ ሕሙማን መኖሪያ ሕንጻ ግንባታ ለመቄዶንያ የበጎ አድራጎት ማኅበር የተደረገው 212.1 ሚሊዮን ብር ድጋፍ ይጠቀሳሉ።

በሳምሶን ገድሉ        

 

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: