Search

1 ሺህ 501ኛው የመውሊድ በዓል "የፍትሑ ነብይ" በሚል መሪ ቃል ይከበራል

ሓሙስ ነሐሴ 14, 2018 96

1 ሺህ 501ኛው የነቢዩ ሙሐመድ የመውሊድ በዓል በመጭው ማክሰኞ በመላው ሀገራችን በድምቀት እንደሚከበር የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት አስታወቀ።

ጠቅላይ ምክር ቤቱ የበዓሉን መከበር አስመልክቶ በሰጠው መግለጫ፣ ሕዝበ ሙስሊሙ የልደት በዓሉን ሲያከብር የነቢዩ ሙሐመድን የበጎነት፣ የፍትሕ እና የሕይወት ፈለግ በመከተል ሊሆን እንደሚገባ ጥሪ አቅርቧል።

በዕለቱ አቅመ-ደካሞችን፣ የተፈናቀሉትን እንዲሁም ድጋፍ የሚያስፈልጋቸውን ወገኖች በመደገፍ፣ በማዕድ ማጋራት እና ለሀገር ሰላም እና አንድነት ዱዓ በማድረግ በዓሉን ማሳለፍ እንደሚገባ መልዕክት አስተላልፏል።

ሰላም፣ ወንድማማችነት እና ይቅር መባባል የማኅበረሰባችን መሠረታዊ እሴቶች መሆናቸውን በመረዳት ሀገራዊ አንድነትን ይበልጥ ማጠናከር እንደሚገባ ጠቅላይ ምክር ቤቱ አሳስቧል።

የእምነቱ ተከታዮች በዓሉን አስተምህሮው በሚያዘው መንፈሳዊ መንገድ ማክበር እንደሚገባቸው የተጠቆመ ሲሆን፣ የዘንድሮውን የመውሊድ በዓል ኢትዮጵያውያን በሀገራዊ ምክክር ሂደት ላይ በሚገኙበት ወቅት መሆኑ ልዩ ያደርገዋል።

በመሆኑም በሀገራችን እያካሄደ ያለው የምክክር ሂደት ውጤታማ ሆኖ በስኬት እንዲጠናቀቅና ዘላቂ ሰላም እንዲረጋገጥ ህዝበ ሙስሊሙ የበኩሉን አወንታዊ ድርሻ እንዲወጣ ጥሪ ቀርቧል።

የዘንድሮው 1 ሺህ 501ኛው የመውሊድ በዓል የነቢዩን አስተምህሮ መሠረት በማድረግ "የፍትሁ ነብይ" በሚል መሪ ቃል በተለያዩ መንፈሳዊ እና ማኅበራዊ መርሐ-ግብሮች ይከበራል።

በመሐሪ ዓለሙ

 

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: