የግል ስሜትን መግራት፣ የጋራ ትዕግስትን መላበስ፣ ህብረትን መዘመር፣ በራስ አቅም ኃይልን ማጎልበት፣ ከፍታን ለበጎ ዓላማ መጠቀም፣ ሀገርን በእኔነት መገንባት እና ፈተናዎችን መልካም እድል የማድረግ ብቃት ጀግንነት ለሚለው መለኪያ ተገቢዎቹ ገለፃዎች ናቸው።
ይህ ይሆን ዘንድ በየዘርፉ የሀገራችንን ድሎች ለማስመዝገብ ብሎም መሠረቱን ለመገንባት ኢትዮጵያ እና ልጆቿ እየመከሩ ይገኛሉ።
በቴክኖሎጂም ሆነ በሁሉም ረገድ በልህቀት በመገኘት ብሎም ድሉን ለማጣጣም ጀግኖች ትልቅ ሚና አላቸው፤ አዎ፣ በዚህ መስመር የተገኙ ሁሉ የድሉ ባለቤቶች ናቸው።
ይህን የሀገራዊ ጀግንነትና የጋራ ከፍታ ጥሪ መነሻ በማድረግ፣ በሀገር ውስጥና በውጭ ሀገራት የሚኖሩ አራት ሺህ ተመካካሪዎች የተሳተፉበት ታሪካዊው ሀገራዊ የምክክር ጉባኤ፣ የጋራ አሸናፊነትን በማረጋገጥ የዚች ምድረ-ቀደምት ሀገር ሁለንተናዊ ከፍታ መሠረት እየጣለ ይገኛል።
በምክክር ሂደቱ የተሳተፉ ተመካካሪዎች ያቀረቡት ሀሳብም በዚህ ሀገራዊ መድረክ ውስጥ የግል ወይም የቡድን አሸናፊነት ሳይሆን፣ ብቸኛዋ አሸናፊ ሀገራችን ኢትዮጵያ ብቻ መሆኗን ማረጋገጥ ነው በሚል አበይት ጭብጥ ላይ ይገናኛል።
ለዘመናት በልዩነቶችና በፖለቲካዊ ውዝግቦች ምክንያት የተከማቹ ቅሬታዎችን በኃይል ወይም በመግፋት ለመፍታት የተደረጉ ጥረቶች ኢትዮጵያን ከፍተኛ ዋጋ ሲያስከፍሉ መቆየታቸው ይታወቃል።
ይህ የምክክር ጉባኤ ግን ያንን የኋላቀር እሳቤ በመቀየር፣ ሀገራዊ ችግሮችን በጠረጴዛ ዙሪያ የመፍታት አዲስ የተግባቦት ባህል እና የፖለቲካ ምዕራፍ በመክፈት ብሔራዊ ጥቅምን ያስቀደመ አዲስ የታሪክ እጥፋት ፈጥሯል።
የዚሁ ታሪካዊ ሂደት አካል የሆኑት ተመካካሪዎች ያለአንዳች የውስጥም ሆነ የውጭ ጣልቃ ገብነት ሀሳባቸውን በነጻነት፣ በስልጣኔ እና በዴሞክራሲያዊ መንገድ ማንጸባረቃቸውን መስክረዋል።
ሂደቱ ሁሉንም የማህበረሰብ ክፍሎችና የሀሳብ መስመሮች ያካተተ በመሆኑ የጉባኤውን ሙሉነትና ተቀባይነት ከፍ አድርጎታል፤ ይህም ለሀገራችን የወደፊት ጉዞ አዎንታዊ እና አካታች ገዢ ትርክት ግንባታ አስተማማኝ መሰረት ጥሏል።
በኮሚሽኑ በተለዩት ስምንት ዐበይት ሀገራዊ አጀንዳዎች ላይ የተካሄደው ጥልቅ ውይይት፣ በህዝቦች መካከል የቆዩ ቅሬታዎችንና አለመግባባቶችን በውይይት በማከም ለዘላቂ ሰላም ጠንካራ መሠረት ጥሏል።
በተጨማሪም ምክክሩ ተመካካሪዎች እርስ በእርስ እንዲደማመጡ፣ አንዱ የሌላውን ስጋትና ሀሳብ እንዲገነዘብ እንዲሁም በልዩነቶች ውስጥ አብሮ የመቆም ጥበብን እንዲያዳብሩ ሰፊ ዕድል በመፍጠር ህብረብሔራዊ አንድነትን በጽኑ መደገፍ የሚያስችል ምቹ ምህዳር ፈጥሯል።
የጉባኤው አወቃቀር፣ የምክክር ሂደቱና የተደረሱት ስምምነቶች ወደ ተግባር ሲቀየሩ፣ የመደማመጥና የመግባባት ባህልን ለቀጣዩ ትውልድ የሚያስረክብ የጽኑ ሀገረ-መንግሥት ግንባታ ድልድይ ሆኖ ያገለግላል።
በምክክር ጉባኤው የተንጸባረቁት የዜጎች ሀሳቦች እንደሚያስገነዝቡት፣ የውይይቱ ዋና ውጤት የትኛውም ወገን የራሱን ሀሳብ ብቻ ጭኖ መውጣቱ ሳይሆን፣ የሁሉም ሀሳብ ተከብሮ የጋራ ድል መመዝገቡ ነው።
ይህ በልህቀትና በሰለጠነ መንገድ የተከናወነ ሀገራዊ ምክክር፣ ለዘመናት በልዩነት ሲፈተን የነበረውን ህዝባዊ አቅም ወደ አንድነት፣ ልማትና ቴክኖሎጂያዊ ዕድገት በማዞር ሁለንተናዊ ብልፅግናን ለማረጋገጥ የሚረዳ ታላቅ ሀገራዊ አቅም ፈጥሯል።
በመሆኑም ጥንታዊቷና ድል አድራጊዋ ምድረ-ቀደምት ኢትዮጵያ በፅኑ ዓለት ላይ ተገንብታ ለወደፊቱ ትውልድ እንድትሻገር የሚያስችል ታሪካዊ መሠረት ተጥሏል።
በሰለሞን ገዳ
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: