Search

የኢነርጂ ዲፕሎማሲ፦ የቀጣናዊ ትሥሥር ምሰሶ

ሓሙስ ነሐሴ 14, 2018 66

የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ከንድፈ ሐሳብ በመሸጋገር በመሠረተ ልማት ትሥሥር ላይ ወደተመሠረተ ተግባራዊ የኢነርጂ ዲፕሎማሲ አድጓል።

ይህ ስትራቴጂያዊ እርምጃ የውኃ፣ የፀሐይ፣ የንፋስ እና የጂኦተርማል ሀብቶችን በማልማት የአፍሪካ ቀንድን ብሎም መላውን አህጉር በኃይል ለማስተሣሠር ያለመ ነው።

በተለይም "ቅድሚያ ለጎረቤት" በሚለው የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ላይ የተመሠረተው ይኸው የኢነርጂ ዲፕሎማሲ፣ የጎረቤት ሀገራትን የልማት ፍላጎት ከኢትዮጵያ የኤሌክትሪክ አቅርቦት ጋር በማስተሣሠር የጋራ ደኅንነትን፣ የፖለቲካ መረጋጋትን እና ቀጣናዊ ውህደትን የሚያረጋግጥ ውጤታማ የጂኦ-ፖለቲካ መሣሪያ ሆኖ እያገለገለ ይገኛል።

ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ መጠናቀቅ በዚህ የቀጣናው የኢነርጂ ትሥሥር ውስጥ አዲስ ታሪካዊ ምዕራፍ ከፍቷል።

የግድቡን ሙሉ ተርባይኖች ወደ ሥራ ማስገባት እንደ ሀገር አጠቃላይ የኃይል ማመንጨት አቅምን ከነበረበት 5 ሺህ ሜጋ ዋት በታች ወደ 10 ሺህ ሜጋ ዋት ገደማ ከፍ አድርጎታል።

ይህ ግዙፍ ፕሮጀክት የዓባይን ተፋሰስ ጂኦ-ፖለቲካዊ ውጥረት ወደ ጋራ ተጠቃሚነት የቀየረ ሲሆን፣ የታችኞቹን ተፋሰስ ሀገራት በተለይም ሱዳንን ከጎርፍ አደጋ በመታደግ የላቀ ሚና እየተጫወተ ነው።

በተጨማሪም ግድቡ የሚያመነጨው ንጹሕ ኃይል የምሥራቅ አፍሪካ ሀገራት ከከፍተኛ ወጪ እና የቅሪተ አካል ነዳጅ ጥገኝነት ተላቅቀው ወደ አምራች ኢንዱስትሪ ኢኮኖሚ እንዲሸጋገሩ ከፍተኛ ዕድል ይፈጥራል።

ይህ ራዕይ በተግባር ተተርጉሞ ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት ለኬንያ፣ ለሱዳን እና ለጂቡቲ የኤሌክትሪክ ኃይል በማቅረብ ላይ ትገኛለች።

በተጨማሪም ለታንዛኒያ በሙከራ ደረጃ ኃይል ማቅረብ የተጀመረ ሲሆን፣ ከደቡብ ሱዳን ጋርም የኃይል ሽያጭ ስምምነት ተፈራርማ ወደ ጥናት ገብታለች።

ባለፈው ዓመት ከተመረተው 29 ሺህ ጊጋዋት ሰዓት በላይ ኃይል ውስጥ 7 በመቶ ያህሉን ለጎረቤት በማቅረብ 118 ሚሊዮን ዶላር በላይ ገቢ ተገኝቷል።

በተለይም ከኬንያ ጋር የተዘረጋው 500 ኪሎቮልት የከፍተኛ ቮልቴጅ መስመር የምሥራቅ አፍሪካን የኃይል ማዕከል ከደቡብ አፍሪካ ጋር የሚያገናኝ አህጉራዊ የጀርባ አጥንት ነው።

የዲፕሎማሲው ስኬት እና "ቅድሚያ ለጎረቤት" መርሕ እውነተኛነት በጉልህ የታየው ሱዳን በውስጥ ግጭት እና በኢኮኖሚ ቀውስ ውስጥ በነበረችበት አስቸጋሪ ጊዜ የኤሌክትሪክ አቅርቦቱ ሳይቋረጥ መቀጠሉ ነው።

ይህ እርምጃ የኢነርጂ አቅርቦትን እንደ ፖለቲካዊ መጫወቻ ከመጠቀም ይልቅ ለዘላቂ ሰላም እና ለጋራ ዕድገት ማረጋገጫነት የዋለ መሆኑን ያረጋግጣል።

ወደፊትም ይህ የኢነርጂ ትሥሥር ከታዳሽ ኃይል እምቅ አቅም አንጻር እጅግ ሰፊ ተስፋን ሰንቋል።

60 ሺህ ሜጋ ዋት በላይ የሚገመት የውኃ፣ የጂኦተርማል፣ የንፋስ እና የፀሐይ ኃይል እምቅ አቅም መኖሩ፣ ይህንን ቀጣናዊ ውህደት ይበልጥ አስተማማኝ ያደርገዋል።

ይህ የማይናጋ የመሠረተ ልማት ትሥሥር የምሥራቅ አፍሪካን ሀገራት የረጅም ጊዜ የጥቅም እና የደኅንነት ቁርኝት ውስጥ ያስገባቸዋል።

በቀጣይም የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ የውኃ እና ኢነርጂ ሚኒስቴር እንዲሁም የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል በጋራ በመቀናጀት የኢነርጂ ስትራቴጂውን ከቀጣናዊ የንግድ እና የደኅንነት ትሥሥር ጋር ይበልጥ በማዋሐድ የጋራ ብልጽግናን ማረጋገጥ ይጠበቅባቸዋል።

በለሚ ታደሰ

 

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: