Search

ለውጥን ያመከኑ ትውልዶች እና ለውጥን ያዋለዱ ጀግኖች

ሓሙስ ነሐሴ 14, 2018 95

ኢትዮጵያ በረዥም ታሪኳ ውስጥ በርካታ የለውጥ ዕድሎችን በእጇ ብታገኝም፣ እነዚህን ወርቃማ አጋጣሚዎች ትውልዶች በአግባቡ ሳይጠቀሙበት በተደጋጋሚ ስታመክን የኖረች ሀገር ናት።

ሀገራችን ዘመናዊ መንግሥት ለመገንባት በሚደረገው ጥረት ውስጥ በርካታ ሐሳባውያን ጀግኖችን አፍርታለች። በተለይም በሃያኛው ክፍለ ዘመን መባቻ ላይ በርካታ የለውጥ ሐዋርያዎች ቢታዩም፣ በተለያዩ ውስጣዊ እና ውጫዊ ምክንያቶች አድማጭ አጥተው ሐሳባቸው እንዲከሽፍ ሆናል።

በዘመናዊቷ ኢትዮጵያ የለውጥ ታሪክ ውስጥ ከፍተኛ ስፍራ ከሚሰጣቸው ሙከራዎች አንዱ የልጅ ኢያሱ ጅማሮ ነው። ልጅ ኢያሱ ገና አልጋ ወራሽ ከሆኑበት ጊዜ ጀምሮ፣ ኢትዮጵያን ወደ ተሻለ አካታች ሥርዓት ለማምጣት ሞክረዋል።

በወቅቱ የነበረውን ነባር እና ግትር አስተሳሰብ በመሞገት የሃይማኖት ብዝኃነትን ለመቀበል እና የባሕል ብዝኃነትን ለማስተናገድ ያደረጉት ጥረት ከዘመኑ እጅግ የራቀ የለውጥ ጅማሮ ነበር። ይሁን እንጂ ይህ ጥረት በአጭሩ መክኖ ቀርቷል።

ከዚህም ባሻገር የለውጥ ሐሳቦች በበርካታ ኢትዮጵያውያን ምሁራን ሲቀነቀኑ ቆይተዋል። በተለይም የለውጥ ሐዋርያ ተብለው የሚጠሩት ታላቁ ሊቅ ነጋድራስ ገብረ ሕይወት ባይከዳኝ በኢትዮጵያ ታሪክ ያመነጯቸው ሐሳቦች ጎልተው ይታያሉ።

ገብረ ሕይወት ከዘመናዊ አስተዳደር፣ ከሕግ እና ከሥርዓት አንጻር በሕግ የምትመራ ሀገር እንድትኖር የሞገቱ ታላቅ ምሁር ነበሩ።

በተመሳሳይ ዶክተር እጓለ ገብረ ዮሐንስ እና ሌሎችም ምሁራን በለውጥ ዙሪያ ያቀነቀኗቸው ሐሳቦች ለለውጥ ጥሪዎች ትልቅ መሠረት ነበሩ።

በዘውዳዊው ሥርዓት ዘመን ታዋቂው ደራሲ ሐዲስ ዓለማየሁ 'ባርያ እና ጌታ በሚባል ነገር ሀገር ሊኖር አይችልም' የሚል ጠንካራ የለውጥ ሐሳብ አቅርበው ነበር።

አምባሳደር ብርሃኑ ድንቄም ለንጉሡ በጻፉት ደብዳቤ የለውጥ ሐሳቦችን በድፍረት በማንሣት፣ ዘውዱን ለራሳቸው አስቀርተው አስተዳደሩን ለሕዝብ በመስጠት የዴሞክራሲ መንፈስ እንዲያስገቡ ሞግተዋል።

ሌሎችም የዘመኑ ታላላቅ ሰዎች ይህንኑ ሐሳብ ቢያስተጋቡም፣ ጥሪያቸው ሰሚ ባለማግኘቱ አየር ላይ በኖ ቀርቷል።

እነዚህ ሁሉ የሰላማዊ ለውጥ ጥሪዎች ሰሚ ባለማግኘታቸው፣ 1953 . በጄኔራል መንግሥቱ ንዋይ እና በወንድማቸው ገርማሜ ንዋይ የተመራ የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራ ተከሰተ።

ምንም እንኳን መንገዱ መፈንቅለ መንግሥት ቢሆንም፣ ይህ የለውጥ ሙከራ ዓላማው ሕገ መንግሥታዊ የዘውዳዊ ሥርዓትን ለመተግበር የታሰበ ነው። ይህ ሙከራ በእንግሊዞች የተገነባውን ዓይነት ሀገር እንዳይፈርስ አድርጎ ለማስቀጠል የሚያስችል እና ሥር ነቀል መፍረስን የሚያስቀር አቅጣጫ ነበረው።

ይህም ሀገራችን ያገኘችውን እጅግ ወሳኝ የለውጥ ዕድል ያጨናገፈ የታሪክ አጋጣሚ ሆኖ ተመዝግቧል። 1953 ግርግር ተብሎ የሚጠቀሰው ክስተት በኢትዮጵያ ከዚያ በኋላ ለመጣው አብዮትና መነቃቃት ሁሉ እንደ መሠረት ሆኖ ቢያገለግልም፣ ጊዜያዊው ዕድል ግን ከስሟል።

የየካቲት 66 አብዮት የሕዝባዊ መንግሥት መመሥረት እና የመሬት ለአራሹ ጥያቄዎችን ይዞ የተነሣ እና የብዙኃንን ድምፅ ያሰማ ነበር። ነገር ግን የለውጥ ፈላጊው ኃይል በሐሳብ ልዩነት መከባበር አቅቶት እርስ በርሱ በመጠፋፋቱ፣ አብዮቱ በጠመንጃ ባነገቡ ወታደሮች ተነጠቀ።

በዚህም ምክንያት 1966 አብዮት አስከፊ አምባገነናዊነትን ወለደ። ትውልድ የራሱን የለውጥ ዕድል ያባከነው ተቻችሎ መወያየትን ባለመቻሉ፣ የሐሳብ ልዩነትን እንደ ወንጀል በመቁጠር እና እርስ በርስ በመጠፋፋቱ ነበር። በዚህም ምክንያት ሌላው ትልቅ የለውጥ አጋጣሚ ክፉኛ ባከነ።

የለውጥ ማክሸፍ የትውልድ ታሪክ እዚህ ላይ አላበቃም። የደርግ ሥርዓት ከወደቀ በኋላ 1983 . በተመሳሳይ ሌላ የለውጥ እና የተስፋ ጭላንጭል የታየበት ዘመን ነበር። ሁሉን አቀፍ ሥርዓት ለመገንባት የሚያስችል የሽግግር ወቅት ተፈጥሮ የነበረ ቢሆንም፣ በሒደት ኢትዮጵያ እንደገና ወደ አምባገነንነት አዘነበለች። የፖለቲካ ምኅዳሩ እየጠበበ ሄዶ፣ የአንድ ፓርቲ አውራነት በመንገሡ ምክንያት ሕዝቡ የሚፈልገው እውነተኛ ለውጥ ሳይመጣ ቀረ።

በተመሳሳይ 1997 . የተካሄደው ሀገራዊ ምርጫ ሰፊ ተስፋ የተጣለበት እና ሌላ የለውጥ ዕድል ይዞ የመጣ ቢሆንም፣ ዳግም ተስፋው ጨለመ። በምርጫው ወቅት የታየው የሕዝብ ተሳትፎ አስደናቂ ቢሆንም፣ ከምርጫው በኋላ በተፈጠረው አለመግባባት፣ ጽንፈኝነት እና አፈና ምክንያት የዴሞክራሲ ምኅዳሩ በድጋሚ ጠበበ።

እነዚህ ሁሉ የታሪክ ማኅደሮች የሚያሳዩት ኢትዮጵያ በተደጋጋሚ በእጇ የገባውን የለውጥ ዕድል በትውልዱ አባካኝነት እያመከነች፣ ዕድሎችን እያጣች መጓዟን ነው።

እንደ ሀገር የለውጥ ሐሳብ ብልጭ ሲል ተረባርበን እያጠፋን፣ በየጊዜው የምናገኘውን ዕድል ስናመክን፣ የለውጥ ብልጭታዎችን እያከሰምን ቆይተናል። በተለይም የእነዚህ ትውልዶች ታሪክ ለውጥን ያከሸፉ ትውልዶች ታሪክ ሆኖ ሲዘከር ቆይቷል።

አሁንስ በእጃችን የገባውን ታሪካዊ ዕድል ምን እያደረግነው ነው? የጥላቻ እና የመጠፋፋት ፖለቲካ ኢትዮጵያን ለዘመናት በጦርነት አዙሪት ውስጥ አቆይቷታል። ይህንን አዙሪት ለመስበር አሁን በእጃችን ላይ ትልቅ የለውጥ ዕድል አለ። ይህ የለውጥ ዕድል ብቻ ሳይሆን፣ በተጨባጭ ለውጥ ያሳየ ባለፉት ስምንት ዓመታት የለውጥ ቆይታ ኢትዮጵያን ከሥረ መሠረቷ የቀየረ፣ አስደናቂ ሥር ነቀል ሪፎርም ያካሄደ የለውጥ ጀግና ትውልድ በኢትዮጵያ መጥቷል።

2010 . ሀገራዊ ለውጥ ኢትዮጵያን ወደ ሉዓላዊነት ከፍታ፣ ስሟን ወደሚመጥን ክብር ስፍራ፣ እና በጣም አስደናቂ የዕድገት ተምሳሌት ውስጥ እየከተታት ያለ እውነተኛ ለውጥ ነው።

ባለፉት ዓመታት የከሸፉትን የለውጥ ዕድሎች በመማር፣ ይህ የመደመር ትውልድ የማይከሽፍ የለውጥ ዕድል ይዞ ተነሥቷል። የመደመር ዕሳቤ ያመጣው ትልቁ ጥበብ፣ ያለፈውን እያፈረሱ ከዜሮ ከመጀመር ይልቅ የትናንትን ስህተት አርሞ፣ ጠንካራውን አስጠብቆ፣ የነገውን ብሩህ ጊዜ መተለም ነው።

ይህ ትውልድ የለውጥ ዕድልን አያመክንም፤ ይልቁንም ለውጥን ያዋለዱ ጀግኖች የሚባሉትን የተግባር ሰዎች ያቀፈ ነው። የመደመር ትውልድ መካረርን፣ ጽንፈኝነትን፣ እና መጠፋፋትን ትቶ፣ በእውነተኛ የኢትዮጵያዊ ዴሞክራሲ እና በመግባባት ላይ የተመሠረተ ሥርዓት ለመገንባት ቆርጦ ተነሥቷል።

ይህ ትውልድ ኢትዮጵያን የብልጽግና እና የሰላም ተምሳሌት ለማድረግ ሌት ተቀን እየሠራ ይገኛል። ኢትዮጵያን ከስንዴ ለማኝነት አላቅቆ ወደ ውጭ ላኪነት ያሸጋገረው፣ ታላቁን የሕዳሴ ግድብ ወደ ማጠናቀቂያው ያደረሰው፣ ከተሞችን ያስዋበው እና የዜጎችን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ያረጋገጠው ይኸው ለውጥን ያዋለደው ጀግና ትውልድ ነው።

ኢትዮጵያ አሁን የተያያዘችው የለውጥ ጉዞ መዳረሻዋን በግልጽ የሚያሳይ ነው። በመደመር ዕሳቤ የሚመራው ይህ ትውልድ የሐሳብ ልዩነትን እንደ በረከት እንጂ እንደ መርገም አይቆጥርም።

አካታች የሆነ ሀገራዊ ምክክር በማድረግ፣ ያለፈውን ቁርሾ በሽግግር ፍትሕ በማከም እና የሲቪክ ባሕልን በማዳበር፣ ጠንካራ እና የማይናወጥ ሀገረ መንግሥት እየገነባ ይገኛል።

የዚህ ዘመን ትውልድ ያገኘው ይህ ዕድል ከምንጊዜውም በላይ በጠንካራ መሠረት ላይ የቆመ፣ ሀገራዊ ብልጽግናን እውን ለማድረግ የተነሣሣ፣ እና ከማንኛውም የፖለቲካ ንትርክ ባለፈ ሀገርን አጽንቶ ወደ ፊት የሚያራምድ ነው። ይህ ለውጥ አሁን በትውልድ እጅ መካከል ያለ የለውጥ ዕድል ነው።

ይህንን ታሪካዊ ለውጥ በደንብ ማስቀጠል፣ መንከባከብ፣ እና መጠበቅ የዚህ ትውልድ ኃላፊነት ነው። የለውጥ ሐሳቦችን በጠንካራ ሥነ ምግባር እና እውነተኛ የሀገር ፍቅር ላይ አንጾ የሚያራምደው ይህ ትውልድ፣ በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ለውጥን ያከሸፉ ሳይሆን ለውጥን ያዋለዱ ተብለው ከሚመዘገቡት የፊት ረድፍ ላይ ይቆማል።

ታሪካዊ ለውጥን የማስቀጠል ጉዞ አሁን በተጨባጭ ተጀምሯል። አዲሱ ትውልድ ያገኘውን ይህን እጅግ ውድ ሀገራዊ ዕድል እንደ ቀደምት ዘመናት አያባክንም። በእጅ ያለውን ወርቅ በማንጠር ሀገርን በክብር ማቆም የሚችል ጀግና ትውልድ መጥቷል።

ይህ የመደመር ትውልድ ሀገረ መንግሥቱን የማጽናት እና የለውጥ ጉዞውን ከዳር የማድረስ አቅም አለው። እኛ የመደመር ትውልዶች ያገኘነውን ይህን በእጅ ያለ ወርቅ ወደ ላቀ የብልጽግና ጌጥ በመቀየር ኢትዮጵያን ለዘላለም በጽኑ መሠረት ላይ እናቆማታለን።

ጽኑ መሪነት እና በሕዝብ ፍላጎት ላይ የተመሠረተ ተግባር ሀገርን ወደ ብሩህ ተስፋ እና ብልጽግና እንደሚወስድ፣ ይህ ትውልድ የጀመረው ጉዞ ሕያው እና ደማቅ ምስክር ነው። ታሪካዊ ዐደራችንን ተወጥተን እናሸንፋለን።

በአዶኒያስ ወልደአረጋይ

 

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: