የኢትዮጵያ ታሪካዊ እና ስትራቴጂያዊ አቀማመጥ ከጥንት ጀምሮ በቀይ ባሕር ቀጣና ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ እንድታሳድር ያስገደዳት ቢሆንም፣ የባሕር ኃይል ግንባታዋ ታሪክ ግን አሳዛኝ የክህደት ጠባሳ ያረፈበት ነበር።
ኢትዮጵያ ጠንካራ የባሕር ኃይል በመገንባት የባሕር ላይ ንግዷን እና ሉዓላዊነቷን በክብር ካስጠበቀችበት ጫፍ ተነሥታ፣ በፖለቲካዊ ውሳኔዎች ኃይሏ ሙሉ በሙሉ ወደ መበተን፣ ታሪካዊ መርከቦቿ ወደ ስብርባሪ ብረትነት ወደ መቀየር፣ እንዲሁም ሀገራችን ወደብ አልባ ወደ መሆን ያዘቀዘቀ አሳዛኝ ታሪክ አስተናግዳለች።
የዘመናዊው የኢትዮጵያ ባሕር ኃይል ታሪክ በቀጥታ የሚያያዘው ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት ማብቃት በኋላ ነው። በ1948 ዓ.ም የኢትዮጵያ ኢምፔሪያል ባሕር ኃይል በይፋ ሲመሠረት፣ በምጽዋ ወደብ ላይ የመጀመሪያው የጦር ሰፈር ተቋቋመ።
በወቅቱ ከፍተኛ የትምህርት ጥራት እና ዓለም አቀፍ ትብብር በማድረግ የባሕር ኃይል ኮሌጅ ተመሥርቶ ብቁ መኮንኖችን አፍርቷል።
በዓለም ታዋቂ ከሆኑት የአሜሪካና የጣሊያን የባሕር ኃይል አካዳሚዎች ሳይቀር እየተላኩ የሠለጠኑት እነዚህ መኮንኖች፣ ኃይሉን በከፍተኛ ዲሲፕሊን አንጸውት ነበር።
"ዘርዓይ ደረስ" እና "ኢትዮጵያ" የተሰኙት ታሪካዊ መርከቦችም በቀይ ባሕር ላይ የኢትዮጵያን ባንዲራ ለመጀመሪያ ጊዜ በማውለብለብ የሀገር ሉዓላዊነት ምልክት ሆነው አገልግለዋል።
በ1966 ዓ.ም የተፈጠረውን የመንግሥት ለውጥ ተከትሎ፣ የኢትዮጵያ ወታደራዊ አጋርነት ወደ ሶቭየት ኅብረት አቅጣጫውን ቀየረ። የባሕር ኃይሉ የድሮ መርከቦች በዘመናዊ የሶቭየት ሚሳኤሎች እና ፈጣን የጥቃት ጀልባዎች ተተኩ።
በአጠቃላይ ከ11 ሺህ በላይ የሰው ኃይል እና በርካታ መርከቦችን ማስተዳደር ችሎ የነበረው ይህ ኃይል፣ በዘመኑ እጅግ ግዙፍ አቅም ፈጥሮ ነበር። ሆኖም፣ በሰሜን ኢትዮጵያ የተቀሰቀሰው የእርስ በርስ ጦርነት የባሕር ኃይሉን ስትራቴጂያዊ ቁመና ፈተና ውስጥ ከተተው።
በ"ኦፕሬሽን ፈንቅል" ዘመቻ በምጽዋ ወደብ ላይ በተከፈተ ጥቃት የኢትዮጵያ ባሕር ኃይል ታላቅ ውድመት አስተናገደ።
በ1983 ዓ.ም የነበረውን ሀገራዊ የፖለቲካ ለውጥ ተከትሎ፣ የኢትዮጵያ ወታደራዊ እና ብሔራዊ ሉዓላዊነት ታሪክ እጅግ ልብ የሚሰብር እና ሀገራዊ ሀብት የጠፋበት ምዕራፍ አስተናገደ።
የቀሩት የባሕር ኃይል መርከቦች የጠላትን እሳት ጥሰው አሰብን ለቅቀው ወደ የመን እና ሳዑዲ ዓረቢያ የባሕር ዳርቻዎች ማምለጥ ቢችሉም፣ የወቅቱ የሽግግር መንግሥት የሀገርን ሉዓላዊነት እና የባሕር ላይ ደኅንነት በማስቀደም የባሕር ኃይሉን በአግባቡ ለመረከብ ፈቃደኛ አልነበረም።
ይህ ተቋማዊ ቸልተኝነት፣ ታሪካዊ መርከቦች ያለምንም ጥገና በውጭ ሀገር ወደቦች እንዲቆሙ አደረገ።
በመጨረሻም በከፍተኛ የሀገር በጀት የተገነቡት፣ የኢትዮጵያ ኩራት የነበሩት መርከቦች ተበጣጥሰው በቆሻሻ ብረትነት ሲሸጡ፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ የሠለጠኑት የባሕር ኃይል መኮንኖችም ለስደት ተዳረጉ።
ጠቅላይ መምሪያው በይፋ ተዘግቶ የባሕር ኃይሉ ሕልውና በአሳዛኝ ሁኔታ አከተመ።
ይህ የባሕር ላይ መገለል እና ፍጹም ወደብ አልባነት ኢትዮጵያን ለተከታታይ አስርት ዓመታት ለከፍተኛ የጂኦፖለቲካዊ እና የሎጂስቲክስ ጫና አጋልጧት ቆይቷል።
ብሔራዊ ደኅንነትን በእጅጉ የሚፈታተነውን ይህንን ስትራቴጂያዊ ስጋት በመገንዘብ፣ በ2010 ዓ.ም የኢትዮጵያን ባሕር ኃይል ዳግም የማቋቋም ታሪካዊ ውሳኔ ተላለፈ።
ይህ እርምጃ ኢትዮጵያ ከብተና ወጥታ ዳግም ብሔራዊ ሉዓላዊነቷን ለማስመለስ የጀመረችው ጉዞ ማሳያ ነበር።
አዲሱ ባሕር ኃይል በ2012 ዓ.ም በይፋ እንደገና ሲዋቀር፣ በዘመናዊ ቴክኖሎጂ እና ዕውቀት ለማስታጠቅ መንግሥት ከፈረንሳይ፣ ከጣሊያን እና ከሩሲያ ጋር ሰፊ ወታደራዊ እና የትምህርት ትብብር ስምምነቶችን ፈጽሟል።
ኢትዮጵያ በቀይ ባሕር ጂኦፖለቲካ ውስጥ ያላትን ተፈጥሯዊ የንግድ መብት፣ የባሕር በር ፍላጎት እና የብሔራዊ ደኅንነት ሕልውና ለማስከበር ጽኑ አቋም ወስዳለች።
ለዚህም ማሳያው ኢትዮጵያ ወደ ቀይ ባሕር ለመመለስ ቁርጠኛ አቋሟን መግለጿ እና ይህንንም ለማስፈጸም በግልጽ መንቀሳቀስ መጀመሯ ነው።
የባሕር ኃይሉን ዳግም ወደ ቀይ ባሕር ለመመለስ የሚደረገው ጥረት፣ የሀገራችንን ሉዓላዊነት ከማንኛውም ጊዜ በላይ የሚያጸና ነው።
የኢትዮጵያ የአሁኑ የቀይ ባሕር አጀንዳ እና የባሕር ኃይል ተልዕኮ፣ ታሪካዊ የጥበቃ ኃላፊነትን ከመወጣት የዘለለ ጥልቅ ራዕይ አለው።
ዳግም የተገነባው ተቋም የማጥቃት ወይም የቀጣናውን ሀገራት የመውረር ዓላማ ያነገበ ሳይሆን፤ ፍጹም አቅም ያለው፣ ለቀጣናው ሰላም እና መረጋጋት አስተማማኝ የጀርባ አጥንት የሚሆን ብርቱ ኃይል ነው።
ጠንካራ የኢትዮጵያ ባሕር ኃይል መገንባት፣ ለአካባቢው ሀገራት ግርማ እና ዋስትና ሆኖ፣ የጋራ ተጠቃሚነትን እና ትብብርን የሚያረጋግጥ ነው።
ይህ ታላቅ ኃይል፣ ለ120 ሚሊዮን ሕዝብ የኢኮኖሚ እና የፖለቲካ ሕልውና ዘብ በመቆም፣ ሀገራችንን ከዳርቻ ጥበቃ ወደ አህጉራዊ የቀጣና የሰላም ዋልታነት እያሸጋገራት ይገኛል።
አዲሱ የኢትዮጵያ ባሕር ኃይል በቀይ ባሕር እና በሕንድ ውቅያኖስ ላይ ያላትን ተፈጥሯዊ የንግድ መስመር ጥበቃ እና ስትራቴጂያዊ ተጽዕኖ ዳግም በማረጋገጥ፣ የሉዓላዊነቷ የማይናወጥ ጠበቃ መሆኑን በተግባር እያሳየ ይገኛል።
በአዶኒያስ ወልደአረጋይ
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: