Search

ለኢትዮጵያ የንጹሕ ኃይል ልማት ቁልፍ ሚና እየተጫወተ ያለው አረንጓዴ ዐሻራ

ሓሙስ ነሐሴ 14, 2018 66

በኢትዮጵያ በየዓመቱ የሚከናወነው የአረንጓዴ ዐሻራ የችግኝ ተከላ የተፈጥሮ አካባቢን ከማከም ባለፈ የሀገራችንን ግዙፍ የኃይል ማመንጫ ፕሮጀክቶች ሕልውና በማስቀጠል ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከተ ነው።

መርሐ ግብሩ የውኃ ኃይል ማመንጫ እና የመስኖ ግድቦች ዋነኛ ስጋት የሆነውን ደለል አፈር ከመከላከል በተጓዳኝ የአፈር ለምነትን በመጠበቅ ቁልፍ ሚና እየተጫወተ ይገኛል።

በየዓመቱ በተራቆቱ ተዳፋት መሬቶች ላይ የሚከናወነው የችግኝ ተከላ በዝናብ ወቅት አፈር እየተሸረሸረ ወደ ግድቦች እንዳይገባ ተፈጥሯዊ ማጣሪያ ሆኖ ያገለግላል።

በተመሳሳይ በወንዝ ተፋሰሶች የሚተከሉት ችግኞችም አፈር በቦታው እንዲረጋ ቆንጥጠው በመያዝ ወደ ግድቦች የሚሄደውን የደለል መጠን በእጅጉ ይቀንሱታል።

ይህም የውኃ ኃይል ማመንጫ ግድቦቻችን ሙሉ አቅማቸውን በመጠቀም ለረጅም ጊዜ ኤሌክትሪክ እንዲያመነጩ ያስችላቸዋል።

የደን ሽፋን ማንሰራራት የደለል ሙሌትን ከመከላከል ባለፈ የከርሰ ምድር ውኃ እንዲያገግም እና ዝናብ ሳይዛባ እንዲጥል በማድረግ ረገድ የጎላ ድርሻ አለው።

በተመሳሳይ የውኃ ምንጮች እንዳይደርቁ በማድረግ ለኃይል ማመንጫ ግድቦች አጥጋቢ እና አስተማማኝ የውኃ ፍሰትን ያረጋግጣል።

ዛፎች ከፍተኛ መጠን ያለው ካርቦን በመሰብሰብ ከባቢ አየርን የሚያክሙ በመሆናቸው የአየር ንብረት መዛባት እና ድርቅ የሚጋርጠውን የታዳሽ ኃይል ልማት ማነቆ ይቀንሳሉ።

በተጨማሪም በተፋሰስ ልማት የተጠበቀ የውኃ ሀብት የሚያመነጨው አስተማማኝ ንጹሕ ኃይል ኢትዮጵያ ወደ አረንጓዴ ኢንዱስትሪ የምታደርገውን ሽግግር የሚፋጥን ነው።

በሀገራችን የሚተከለው እያንዳንዱ ችግኝ ሕዳሴ እና ኮይሻን ጨምሮ ግድቦቻችን ነገ ለሚያመነጩት ኤሌክትሪክ እና ለኢኮኖሚው ተጨማሪ አቅም መሆኑን ልብ ይሏል።

በሐና ምንዳሁን

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: