Search

የንጹሕ ኢነርጂ አብዮት፦ የኃይል ማዕከል እና የጤናማ ከተሞች መገኛ እየሆነች ያለችው ኢትዮጵያ

ሓሙስ ነሐሴ 14, 2018 66

ዓለማችን የኃይል ምንጭ አጠቃቀሟን ከበካይ ማዕድናት ወደ ታዳሽ እና ንጹሕ አማራጮች እያሸጋገረች ባለችበት በዚህ ዘመን፣ ኢትዮጵያ የተፈጥሮ ፀጋዋን ወደ ጂኦ-ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ አቅም በመቀየር ላይ ትገኛለች።

ሀገራችን 45 ሺህ ሜጋ ዋት በላይ የውኃ ኃይል የማመንጨት አቅም ያላት ሲሆን፣ 5 ሺህ 150 ሜጋ ዋት በላይ የማመንጨት አቅም ያለውን ታላቁን የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብን ጨምሮ የጊቤ እና ሌሎች ግድቦች የኃይል አቅሟን በእጅጉ አሳድገውታል።

ይህ ሀገራዊ አቅም ለውስጥ ፍጆታ ብቻ ሳይሆን ለጅቡቲ፣ ለሱዳን እና ለኬንያ ኤሌክትሪክ በማቅረብ ኢትዮጵያን የምስራቅ አፍሪካ የኃይል ማዕከል እያደረጋት ነው።

ይህን የኃይል አቅርቦት እስከ ታንዛኒያ እና ደቡብ አፍሪካ ለማስፋት የተያዘው ዕቅድም ቀጣናውን በኢኮኖሚ ከማስተሳሰር ባሻገር ከኃይል ሽያጭ የሚገኘውን የውጭ ምንዛሬ ገቢ ለማሳደግ አስተማማኝ መሠረት ጥሏል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (/)ኢትዮጵያ ውስጥ እንዲመጣ የምናስበው ዕድገት ተፈጥሮን በሚጎዳ መልክ ሳይሆን ተፈጥሮን ሳንነካ የሚረጋገጥ ዕድገት ማምጣት ነው፤ ለዚያ ሁነኛው መድኃኒት ደግሞ ንጹሕ ኢነርጂ ላይ ማተኮር ነውሲሉ የገለጹት ሀሳብ ኢትዮጵያ የአፍሪካን የኃይል ትስስር ራዕይ እውን ለማድረግ ያላትን ቁርጠኝነት የሚያሳይ ነው።

ከውኃ ኃይል በተጨማሪ እየተከናወኑ ያሉ 1 ሺህ 300 ጊጋ ዋት በላይ የንፋስ እንዲሁም የፀሐይ እና ጂኦተርማል የኃይል ፕሮጀክቶች በዓለም አቀፍ ደረጃ የካርቦን ልቀትን ለመቀነስ በሚደረገው ጥረት ኢትዮጵያ የራሷን አሻራ እንድታኖር አስችለዋታል።

ከታዳሽ ኃይል ልማቱ ጎን ለጎን በአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር አረንጓዴ ኢኮኖሚ ለመገንባት የተጀመረው ጉዞም ዓለም አቀፍ እውቅናን እያተረፈ ይገኛል።

በተለይም አረንጓዴ አሻራን ከምግብ ዋስትና ጋር በማስተሳሰር በበጋ መስኖ ስንዴ ልማት የተመዘገበው ስኬት ሀገራችንን ከእርዳታ ጠባቂነት ወደ ላኪነት በማሸጋገር ለሌሎች አዳጊ ሀገራት አርዓያ ያደረጋት ሲሆን፣ ይህን ስኬት ተከትሎም 32ኛውን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የአየር ንብረት ጉባኤ (COP32) እንድታስተናግድ መመረጧ ትልቅ የዲፕሎማሲ ድል ነው።

በሌላ በኩል በአረንጓዴ ትራንስፖርት ዘርፍ ወደ ሀገር ውስጥ የሚገቡ አዳዲስ ተሽከርካሪዎች የኤሌክትሪክ እንዲሆኑ መበረታታታቸው፣ ያረጁ የነዳጅ ተሽከርካሪዎች ከአገልግሎት እንዲወጡ መደረጉ እና በከተሞች እየተገነቡ ያሉ ዘመናዊ የእግረኛና የብስክሌት ኮሪደሮች የሀገር ሀብት ብክነትን ከመግታት ባሻገር ጤናማ ከተሞችን ለመፍጠር አስችለዋል።

ከታላላቅ ግድቦች እስከ ዘመናዊ ግብርና፣ ከፀሐይ ኃይል እስከ ኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች እየተተገበሩ ያሉ ሥራዎች ኢትዮጵያ የነገዋን ብልፅግና በፀና መሠረት ላይ እያቆመች መሆኗን የሚያረጋግጡ ናቸው።

በበረከት ሽመልስ

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: