Search

የኢትዮጵያ አረንጓዴ የትራንስፖርት አብዮት

ሓሙስ ነሐሴ 14, 2018 86

የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል እና የማክሮ ኢኮኖሚ ጫናን ለመቀነስ፣ ኢትዮጵያ በጥር ወር 2016 . በነዳጅ የሚሠሩ የቤት አውቶሞቢሎችን ወደ ሀገር ውስጥ ማስገባትን በማገድ በዓለም የመጀመሪያዋ ሆናለች።

ይህ ቆራጥ የፖሊሲ ውሳኔ ኢትዮጵያ እየገነባች ካለው የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ስትራቴጂ እና ካላት ሰፊ የታዳሽ ኃይል አቅም ጋር በጥብቅ የተቆራኘ ነው።

ኢትዮጵያ በየዓመቱ ለነዳጅ ግዢ 4 ቢሊዮን ዶላር በላይ የውጭ ምንዛሬ ታወጣለች። በሌላ በኩል ደግሞ ከውኃ፣ ከነፋስ እና ከጂኦተርማል ኃይል ማመንጫዎች በተለይም ከታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የምታገኘው ንፁህ እና ርካሽ የኤሌክትሪክ ኃይል አላት።

ይህንን ውድ የሆነ የነዳጅ ወጪ በሀገር ውስጥ ርካሽ ታዳሽ ኃይል ለመተካት፣ ወደ ኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች መሸጋገር አማራጭ የሌለው የመፍትሔ እርምጃ ሆኗል።

ነዳጅ ከውድነቱም በላይ አካባቢን በመበከል ለአየር ንብረት ለውጥ ከፍተኛ ድርሻ የሚይዝ ሲሆን፣ ይህ ደግሞ ኢትዮጵያ ከተያያዘችው የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ግንባታ ጋር የሚጣረስ ነው።

እገዳውን ተከትሎ በአዲስ አበባ እና በሌሎች ከተሞች የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች ሥርጭት በከፍተኛ ፍጥነት እያደገ ነው።

የትራንስፖርት እና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴር መረጃዎች እንደሚያሳዩት አሁን ላይ በመንገዶች ላይ የሚንቀሳቀሱት የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች ብዛት በከፍተኛ ፍጥነት እየጨመረ ነው።

ይህ ለውጥ በተለይ በአዲስ አበባ ከተማ የሕዝብ ትራንስፖርት ላይ መዋቅራዊ መሻሻል አምጥቷል። የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደርን ጨምሮ የተለያዩ የግል ትራንስፖርት ኩባንያዎች በመቶዎች የሚቆጠሩ የኤሌክትሪክ አውቶቡሶችን እና ሚኒባሶችን በማሰማራት አገልግሎት እየሰጡ ይገኛሉ።

የኤሌክትሪክ ቻርጅ ማደያዎች ቁጥርም ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ በመምጣቱ የከተማዋን አየር ብክለት ከመቀነሱም ባለፈ የተሽከርካሪ ባለቤቶች ከፍተኛ የነዳጅ እና የጥገና ወጪን ማዳን ችለዋል።

የፖሊሲ ማበረታቻዎች እና የሀገር ውስጥ አምራቾች ተሳትፎ ኢትዮጵያ ተሽከርካሪዎቹን በማስገባት ብቻ ሳትወሰን በሀገር ውስጥ የማምረት እና የመገጣጠም አቅምን ለማሳደግ ታሪካዊ የታክስ ማሻሻያዎችን አድርጋለች።

ሙሉ በሙሉ ያልተገጣጠሙ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎችን አምጥተው ሀገር ውስጥ ለሚገጣጥሙ አምራቾች (CKD) ከጉምሩክ፣ ከኤክሳይዝ እና ከተጨማሪ ዕሴት ታክስ ነጻ የሆነ ጠንካራ ማበረታቻ ተሰጥቷል። በከፊል ለሚገጣጠሙ 5 በመቶ፤ ሙሉ ለሙሉ ተገጣጥመው ለሚመጡት ደግሞ 15 በመቶ ቀረጥ ብቻ ተጥሏል።

ይህ የፖሊሲ ማዕቀፍ ትላልቅ ኢንቨስተሮችን ወደ ዘርፉ ስቧል። በላይነህ ክንዴ ግሩፕ በደብረ ብርሃን ከተማ በገነባው ፋብሪካ በዓመት 1 ሺህ በላይ ተሽከርካሪዎችን የመገጣጠም አቅም ፈጥሯል። በዚህም ለአዲስ አበባ ከተማ በርካታ ሚኒባሶችን እና ትልልቅ አውቶቡሶችን አቅርቧል።

በተመሳሳይ ግሪን ቴክ አፍሪካ በሰንዳፋ በገነባው ማምረቻው የሕዝብ ቻርጅ ማደያዎችን በመገንባት ላይ ይገኛል። ይህ እንቅስቃሴ ለበርካታ ዜጎች ሰፊ የሥራ ዕድል ፈጥሯል።

ኢትዮጵያ እስከ 2030 ድረስ በመላው ሀገራችን 60 የመገጣጠሚያ ፋብሪካዎችን የመገንባት እና የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎችን ቁጥር ወደ ግማሽ ሚሊዮን ለማድረስ ትልቅ ራዕይ ሰንቃለች።

ይህንን ግብ ለማሳካት ግን አሁን በአዲስ አበባ ብቻ ያተኮሩትን የቻርጅ ማደያ መሠረተ ልማቶች ወደ ሌሎች ከተሞች እና ክልሎች ለማስፋፋት በልዩ ትኩረት እየተሠራ ይገኛል።

የኤሌክትሪክ አቅርቦት ተደራሽነትን ማሳደግ፣ ከኢንሹራንስ ሽፋን እና ከመለዋወጫ ዕቃዎች አቅርቦት ጋር ተያይዘው ያሉ ክፍተቶችን መፍታት ትኩረት ከተሰጣቸው ጉዳዮች መካከል ናቸው።

ኢትዮጵያ የጀመረችው ይህ አረንጓዴ የትራንስፖርት ጉዞ ዓለም አቀፍ አርአያነት ያለው እና ዘላቂ የኢኮኖሚ ዕድገትን የሚያረጋግጥ ታሪካዊ እርምጃ ነው።

በለሚ ታደሰ

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: