ቆሞ ቀሩ እና ሕገ ወጡ የህወሓት ቡድን ከተመሠረተበት ጊዜ ጀምሮ አምባገነን ድርጅት መሆኑን የትግራይ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ትዴፓ) አመራር አቶ ተሻለ ንጉሴ ገልጸዋል።
ሕገ ወጡ ቡድን በ1983 ዓ.ም. የመንግሥት ሥልጣን እንደያዘ ያደረገው ዋና ሥራ በቤተሰብ ደረጃ ቁልፍ የሥልጣን ቦታዎችን መሻማት እንደነበር አቶ ተሻለ አስታውሰዋል።
ይህም በኢትዮጵያ አዲስ ከበርቴ መፍጠር የጀመረበት አሠራር ሲሆን፣ ላለፉት 27 ዓመታት የዘረፈውን ሀብት የእነሱን አስተሳሰብ በሚደግፉ አካላት ዘንድ በማከማቸት ሥልጣኑን ለማራዘም ከመሥራት ባለፈ አዲስ ሐሳብ መቀበል እንደማይፈልግ አስረድተዋል።
መግደል፣ ማዋጋት እና ለሥልጣኑ አደጋ መስሎ የታየውን ሁሉ ማፈን የቡድኑ ተራ እና የዕድሜ ዘመኑ ሥራ መሆኑንም ጠቁመዋል።
በሌላ በኩል በአሁኑ ሰዓት የትግራይ ወጣቶች የሚያስፈልጋቸው ሰላም፣ ልማት፣ የመረዳዳት እና የመግባባት ሁኔታ ብቻ እንደሆነ ለውጥ ፈላጊው ወጣት አለማየሁ አብራርቷል።
ወጣቱ ያላመነበትን ጦርነት በኃይል እንዲገባ ቢደረግ ያለው አንድ አማራጭ በሰላማዊ መንገድ እጅ መስጠት እንደሆነ እና በኃይል አስገድዶ ለውጥ ማምጣት እንደማይቻል ገልጿል።
ወጣቱ በኢትዮጵያዊነቱ የማይደራደር በመሆኑ፣ አሁን ሕገ ወጡ የህወሓት ቡድን እያደረገ ባለው አስገዳጅ አፈሳና አፈና ምክንያት አልታፈስም በማለት ሰላም ወዳለበት አካባቢ እንደሚሄድ ተናግሯል።
በመሆኑም የትግራይ ሕዝብ “ጦርነት አንፈልግም፤ ይብቃን” እያለ በአደባባይ ድምጹን እያሰማ በመሆኑ ሁሉም አካል ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ ጥሪ አቅርቧል።
በጎሳዬ ገ/ኪዳን
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: