Search

የምሥራቅ አፍሪካ የኃይል ትስስር (EAPP) እና የኢትዮጵያ ስትራቴጂያዊ ሚና

ሓሙስ ነሐሴ 14, 2018 75

የምሥራቅ አፍሪካ ሀገራት የኢኮኖሚ ዕድገት እና የኢንዱስትሪዎች መስፋፋት አስተማማኝ የኃይል አቅርቦትን እጅግ ወሳኝ አድርጎታል።

ይህንን ፍላጎት በዘላቂነት ለማሟላት እና በሀገራት መካከል የኃይል ትስስር ለመፍጠር ... 2005 የምሥራቅ አፍሪካ የኃይል ትስስር (East African Power Pool - EAPP) ተመስርቷል።

ድርጅቱ 13 አባል ሀገራትን ያካተተ የቀጣናዊ ትብብር ተቋም ሲሆን፣ ዋና ዓላማው የኤሌክትሪክ አቅርቦትን በማስተሳሰር የኃይል ደኅንነትን ማጠናከር፣ የኃይል ወጪን መቀነስ እና በአጎራባች ሀገራት መካከል ኢኮኖሚያዊ ትስስርን ማሳደግ ነው።

ድርጅቱ ዓላማዎቹን ለማሳካትም አራት ዋና ዋና ማዕቀፎች ላይ ትኩረት አድርጎ ይንቀሳቀሳል፡፡

ድበር ተሻጋሪ የኃይል ንግድ እንዲኖር በማድረግ አነስተኛ የማምረቻ ወጪ ያላቸው ሀገራት ከፍተኛ የወጪ ጫና ላለባቸው ሀገራት በቅናሽ ዋጋ ኤሌክትሪክ እንዲሸጡ ያስችላል።

 በሌላ በኩል በአንድ አባል ሀገር የኃይል እጥረት ወይም የድርቅ አደጋ ቢከሰት ከጎረቤት ሀገራት በፍጥነት ኃይል እንዲተካ በማድረግ የኃይል መቋረጥን ይከላከላል።

 በተጨማሪ በክልሉ ያሉትን የውሃ፣ የንፋስ፣ የጂኦተርማል እና የፀሐይ ኃይል ሀብቶች በጋራና በቅንጅት ለማልማት ያስችላል።

ቀጣናዊ የኃይል መስመሮች እና ግዙፍ ፕሮጀክቶችም ለዓለም አቀፍ አበዳሪዎች እና የግል ባለሀብቶች ይበልጥ ሳቢ እንዲሆኑ በር ይከፍታል።

ኢትዮጵያ ሰፊ የውኃ፣ ንፋስ እና የጂኦተርማል ኃይል አቅም ያላት በመሆኗ በበድርጅቱ ውስጥ የኃይል ምንጭ ማዕከል (Power Hub) በመሆን ታገለግላለች።

 ከሱዳን፣ ከጂቡቲ እና ከኬንያ ጋር የተዘረጉት ከፍተኛ የቮልቴጅ ማስተላለፊያ መስመሮችም የምሥራቅ አፍሪካ የኃይል ትስስር (EAPP) አውታር የጀርባ አጥንት ሆነው ያገለግላሉ።

በኢትዮጵያ-ኬንያ የኃይል መስመር አማካኝነት የድርጅቱ አውታር ወደ ታንዛኒያ አልፎም ወደ ደቡብ አፍሪካ የኃይል ትስስር (SAPP) እንዲገናኝ ሰፊ በር ከፍቷል።

የምሥራቅ አፍሪካ የኃይል ትስስር (EAPP) የቀጣናውን የኢኮኖሚ ትስስር የሚያጠናክር ሲሆን፣ ኢትዮጵያም የአረንጓዴ ኃይል ምንጭ በመሆን የቀጣናውን የኢነርጂ ፍላጎት በመደገፍ ረገድ ግንባር ቀደም ድርሻዋን እየተወጣች ትገኛለች።

ኢትዮጵያ በምሥራቅ አፍሪካ የኃይል ትስስር (EAPP) ውስጥ በመሳተፏ እና ኃይል ወደ ጎረቤት ሀገራት በመላኳም አስተማማኝ እና ዘላቂ የውጭ ምንዛሬ ማስገኘት ችላለች።

 የቀጣናው ሀገራት በኃይል አቅርቦት ላይ በኢትዮጵያ ላይ ጥገኛ መሆናቸው ደግሞ ሀገራችን በምሥራቅ አፍሪካ ያላትን ፖለቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ ተፅዕኖ እና ወዳጅነትም በእጅጉ ያጠናክራል።

በዓይናለም ሃድራ

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: