የኢትዮጵያ የ7 ሚሊዮን ኮደሮች ኢኒሼቲቭ ከመደበኛው የዲጂታል ክህሎት ስልጠና ባለፈ አለም አቀፍ ተፅዕኖ ለመፍጠር ትልቅ ራዕይ የተሰነቀበት ሌላው የነገይቱ ኢትዮጵያ አዲስ ገፅታ ነው።
ኢትዮጵያ በአፍሪካ ደረጃ ትልቅ የህዝብ ቁጥር ያላት ሀገር እንደመሆኗ መጠን የዲጂታል ኢኮኖሚዋ መጎልበት በምስራቅ አፍሪካና በመላው አህጉሪቱ ላይ ያላትን የፖለቲካ እና የኢኮኖሚ ተፅዕኖ ከፍተኛ ያደርገዋል።
ይህ ታላቅ ፕሮጀክት ኢትዮጵያን ከቴክኖሎጂ ተጠቃሚነት ብቻ አውጥቶ ወደ ዋና የቴክኖሎጂ እና የዲጂታል አገልግሎት አቅራቢነት ለማሸጋገር የታለመ አለም አቀፍ ድልድይ ነው።
እንደ ጎግል፣ ማይክሮሶፍት እና አማዞን ያሉ ግዙፍ የቴክኖሎጂ ኩባንያዎች ኢንቨስት የሚያደርጉት የሰለጠነ የሰው ኃይል ባለበት ሀገር በመሆኑ፣ በኢትዮጵያ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ የቴክኖሎጂ እውቀት ያላቸው ወጣቶች መፈጠራቸው ሀገራችንን በአፍሪካ ተወዳዳሪ የቴክኖሎጂ ማዕከል በማድረግ የዓለም አቀፍ ኩባንያዎችን ትኩረት እንድትስብ ያስችላታል።
በተጨማሪም ስልጠናው በዓለም አቀፍ ደረጃ ተቀባይነት ባለው መልኩ የሚሰጥ በመሆኑ፣ ተመራቂዎች የሚያገኙት ሰርተፍኬት በየትኛውም የዓለም ክፍል ተቀባይነት ያለውና በዓለም አቀፍ የስራ ገበያ ተወዳዳሪ የሚያደርጋቸው ነው።
የሶፍትዌር እና የቴክኖሎጂ አገልግሎቶችን ወደ ሌሎች የአፍሪካ አገራት ለሽያጭ ለማቅረብም ሰፊ ዕድል ይፈጥራል።
“የምንናገረው ለመፈጸም ነው” እንዳሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)፣ በእርግጥም በዚህ ኢኒሼቲቭ ኢትዮጵያ በአጭር ጊዜ ከታሰበው በላይ በማሳካት ቃሏን ጠብቃለች፣ የዕድገት ግስጋሴዋንም በአስተማማኝ ሁኔታ ቀጥላለች።
በዓይናለም ሃድራ
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: