በደቡብ ጎንደር ዞን ስማዳ ወረዳ ከዋና ከተማዋ ወገዳ የአንድ ሰዓት የእግር መንገድ ያህል ራቅ ብላ በተራሮች እቅፍ ውስጥ የምትገኘው አራጣ የተሰኘች ጥንታዊት መንደር ታሪኳም ገጿም ብዙ ነው።
ይህች መንደር በአገራችን የታሪክ ድርሳናት ውስጥ ወደር የማይገኝለት እጅግ አስደናቂ የአንድነትና የመቻቻል ታሪክ አቅፋ ይዛለች።
የዚህች መንደር ስያሜ በ12ኛው ክፍለ ዘመን አካባቢ በነበሩት ታላቁ እስላማዊ ሊቅ ጌታው ሼህ ቀሪብ አህመድ የተመሰረተ ነው።
እኚህ ታላቅ ሰው የዘመኑን ንጉሥ ልጅ በማከም ከሞት በማዳናቸው ምክንያት የአካባቢው ነዋሪ ሙሉ በሙሉ ከግብር ነፃ እንዲሆን በማድረጋቸው መንደሯ ይህንን ስያሜ ልታገኝ ችላለች።
በዚህች ጥንታዊት ምድር ላይ ከ12ኛው ክፍለ ዘመን ጀምሮ በቅዳሴና በአዛን፣ በሶላትና በስግደት አምላካቸውን ጎን ለጎን የሚማለዱበት ጥንታዊው የአራጣው ሼህ ቀሪብ አህመድ መስጅድ እና የመካነ ሰላም አራጣ ገብርኤል ገዳም በፍቅርና በሰላም ዘልቀዋል።
እነዚህ በተመሳሳይ የሕንፃ ጥበብ የተገነቡ የእምነት ተቋማት የአካባቢው ሙስሊምና ክርስቲያን ማህበረሰብ በጋራ ደቦ በመውጣት፣ አሸዋ ተሸክመው፣ ድንጋይ ጠርበውና ሲሚንቶ አቡክተው በአንድነት ያቆሟቸው የፍቅር ማሳያዎች ናቸው።
በአራጣ መንደር የእናንተና የእኛ የሚባል የሃይማኖት ልዩነት የለም፤ ይልቁንም ሙስሊሙና ክርስቲያኑ በኢድ፣ በመውሊድ፣ በአረፋ፣ በትንሣኤ፣ በመስቀልና በጥምቀት በዓላት ወቅት ደስታቸውን በጥብቅ ወንድማማችነት በጋራ ያሳልፋሉ።
አንዱ የእምነት ተከታይ የሌላውን እምነት ከማክበር አልፎ የሌላኛውን ታሪክና ቅርስ ጠብቆ እስከማቆየት የደረሰበት ይህ መስተጋብር፣ አራጣን በምግባር የገዘፈች የኢትዮጵያውያን የጋራ እሴት ተምሳሌት አድርጓታል።
የመንደሯ መሥራች የሆኑት ሼህ ቀሪብ አህመድ ከ500 በላይ ደረሳዎችን ያፈሩ ታላቅ የሃይማኖት አባት ብቻ ሳይሆኑ፣ በሕክምና፣ በሳይንስና በጥንታዊ የሥነ-ፈለክ (አስትሮኖሚ) ምርምር ረቂቅ መጻሕፍትን በመጻፍ የጎሉ ድንቅ ምሁር እንዲሁም የነገሥታት አማካሪ ነበሩ።
ታዲያ ይህንን ግዙፍ ታሪካዊ አሻራ የጣሉትን ታላቅ ሰው ምስል በሌላ ስፍራ ማግኘት ባይቻልም፣ በ12ኛው ክፍለ ዘመን በተቆረቆረው ጥንታዊው መካነ ሰላም አራጣ ገብርኤል ገዳም የውስጥ ግድግዳ ላይ ግን በእጅ የተሳለ ምስላቸው ይገኛል።
በአፄ እያሱ ዘመነ መንግሥት እንደተሳለ ከግርጌው የተቀመጠው የዓመተ ምህረት መረጃ የሚያስረዳው ይህ የሼህ ቀሪብ አህመድ ምስል፣ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ጠባቂነት ለ4 ክፍለ ዘመናት በሙሉ ክብርና እንክብካቤ ተጠብቆ ለዛሬው ትውልድና ለጎብኚዎች ሲታይ የአካባቢውን ህዝብ የወንድማማችነት ጥልቀት በግልጽ ያሳያል።
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: