Search

የምክክር ጉባኤው የጋራ ትርክት በመፍጠር የነገዋን ኢትዮጵያ ለመገንባት መሠረት ጥሏል - ተመካካሪዎች

ቅዳሜ ነሐሴ 16, 2018 97

በኢትዮጵያ ሀገራዊ የምክክር ጉባኤ ላይ እየተሳተፉ የሚገኙ ተመካካሪዎች፣ የምክክር ሂደቱ ልዩነቶችን በማጥበብ እና የጋራ ትርክት በመፍጠር ለነገው ትውልድ የምትሻገር ጠንካራ ኢትዮጵያን ለመገንባት ጽኑ መሠረት የጣለ መሆኑን ገለጹ።

ተመካካሪዎች እንዳብራሩት፣ ሀገራችን በጋራ ማደግ እና መራመድ ስትችል በእርስ በርስ ግጭቶች እና በመጠላላት ብዙ ዋጋ የከፈለችባቸው ጊዜያት ሊያበቁ ይገባል።

የብሔር ልዩነትን የሚያጎሉ አጉል ትርክቶችን ወደ ጎን በመተው፣ በጋራ የምንኖርባት እና የምናድግባት ኢትዮጵያን ለመገንባት መድረኩ ትልቅ ተስፋ የፈጠረ መሆኑን ገልጸዋል።

በመሆኑም ተሳታፊዎች የግል ፍላጎቶቻቸውን በመተው፣ መጪውን ትውልድ ማዕከል ያደረገ እና ሀገርን በዘላቂነት ሊያሻግሩ በሚችሉ ሐሳቦች ላይ በስፋት መምከራቸውን አስረድተዋል።

ሂደቱ እጅግ ዴሞክራሲያዊ እና ነፃ መሆኑን ያነሡት ተመካካሪዎቹ፣ የኢትዮጵያን የወደፊት ዕጣ ፈንታ በሚወስኑ እንዲሁም ሰላምን እና ዴሞክራሲን በሚያሰፍኑ ወሳኝ የሀገር ግንባታ ጉዳዮች ላይ በግልጽ መወያየት መቻላቸውን ጠቁመዋል።

ከተለያዩ የሀገራችን ክፍሎች የመጡ ዜጎች በአንድ ላይ ቁጭ ብለው በመነጋገር ችግሮችን መፍታት መቻላቸው፣ ወጣቱ ትውልድ ሀገሩን እንዴት ማስቀጠል እንዳለበት ጠንካራ መሠረት የጣለ እና ለሀገራችንም ብሩህ ተስፋን የፈነጠቀ መሆኑን አብራርተዋል።

የምክክሩ ዋነኛ ዓላማ ሀገር ግንባታ መሆኑን ያነሡት አስተያየት ሰጪዎች፣ ውይይቶቹ ከዐሥር ሰዎች ጀምሮ ወደ ሃምሳ፣ ሁለት መቶ ሃምሳ እና አምስት መቶ ተሳታፊዎች ወዳሏቸው ቡድኖች እያደጉ መምጣታቸው፣ የመደማመጥ ባህልን በማዳበር የሐሳብ ልዩነቶችን ይበልጥ ለማጥበብ ትልቅ ሚና መጫወቱን አስገንዝበዋል።

እንደ አንድ ቤተሰብ በመደማመጥ በተካሄደው በዚህ ሂደት ውስጥ ዋናው ግብ ልዩነቶችን አጥብቦ ሀገራዊ አንድነትን ማጠናከር እንደሆነ ነው የተናገሩት።

ከታች ጀምሮ የተሰበሰቡት የሕዝብ አጀንዳዎች ተጠናቅረው በወጡት ስምንት ዋና ዋና ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ሰፊ ውይይት መደረጉን ተሳታፊዎቹ ገልጸዋል።

ከዚህ ታሪካዊ መድረክ የሚመነጩት ምክረ ሐሳቦች እንደ ፖሊሲ ሊያገለግሉ የሚችሉ መሆናቸውን በመጠቆም፣ መንግሥት እነዚህን ሐሳቦች በጥንቃቄ ወስዶ ቅድሚያ ለሚሰጣቸው ጉዳዮች ትኩረት በማድረግ ተግባራዊ እንዲያደርጋቸው ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል።

በዮናስ በድሉ

 

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: