በኢትዮጵያ በቅርብ ዓመታት እየተመዘገቡ ያሉ ግዙፍ የልማት ስኬቶች የሀገራችንን ገጽታ በከፍተኛ ደረጃ እየቀየሩ ይገኛሉ።
ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ፣ ዘመናዊ የፍጥነት መንገዶች፣ የኮሪደር ልማቶች እንዲሁም የቀጣናዊ ትስስር እና የባሕር በር ስትራቴጂዎቻችን የኢኮኖሚ ዕድገታችን ጉልህ ማሳያዎች ናቸው።
ነገር ግን ከነዚህ ግዙፍ የኮንክሪት፣ የአስፋልት ግንባታዎች እና ስትራቴጂዎች ጀርባ ያለው ዋና የልማት ግብ ምንድነው?
የዚህ ጥያቄ ምላሽ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) “መደመር”፣ “የመደመር መንገድ”፣ “የመደመር ትውልድ” እና “የመደመር መንግሥት” መጻሕፍት ውስጥ በግልጽ ተብራርቷል።
ዋናው መልዕክትም “ሰውን የዘነጋ ልማት የጥፋት ያህል ነው” የሚለው መርህ ነው። የቱንም ያህል ግዙፍ ፕሮጀክት ቢገነባ የዜጎችን የዕለት ማዕድ ካልቀየረ፣ የሕፃናትን ዕድገት ካላረጋገጠ እና ለችግር የተጋለጡትን ክብር ካልጠበቀ ዕድገቱ ፍትሐዊ እና ዘላቂ ሊሆን አይችልም። ልማት ትክክለኛ ትርጉም የሚያገኘው የሰዎችን ዕንባ ማበስ ሲችል ብቻ ነው።
ለረጅም ዘመናት የተሞከሩ የፖለቲካ ርዕዮተ-ዓለሞች የሥልጣን ሽኩቻን ያስቀደሙ እንጂ የሰውን ልጅ ሁለንተናዊ ፍላጎት ማዕከል ያደረጉ አልነበሩም።
በአንጻሩ የመደመር እሳቤ የኢትዮጵያን ባህል እና ማኅበራዊ መሠረት ያገናዘበ ሀገር በቀል መፍትሔ ነው።
ይህ ፍልስፍና የልማት ትርጓሜን ከቁጥራዊ የኢኮኖሚ (GDP) ዕድገት ባሻገር የእያንዳንዱን ዜጋ የኑሮ ጥራት ወደ ማሻሻል እና ማኅበራዊ ፍትሕን ወደ ማስፈን አሸጋግሮታል።
የመደመር እሳቤ በወረቀት ላይ የሰፈረ ጽንሰ-ሀሳብ ብቻ አይደለም። መጽሐፍቱ ለሕትመት ከበቁ በኋላ ከሽያጭ የተገኘው በቢሊዮኖች የሚቆጠር ገቢ ሙሉ በሙሉ ለሰው ተኮር ልማት እንዲውል ተደርጓል።
ከዚህ ገቢ በተሠሩ ዘመናዊ የትምህርት ቤት ማዕከላት በርካታ ተማሪዎች ምቹ መማሪያ አግኝተዋል። በተጨማሪም የመደመርን ፍልስፍና መሠረት በማድረግ በሺዎች የሚቆጠሩ ተማሪዎችን የሚመግበው ፕሮግራም፣ የታላቁ አብርሆት ቤተ-መጽሐፍት፣ የገበታ ለሀገር እና የሸገር ፕሮጀክቶች እውን ሆነዋል። ይህ እሳቤ ተሽጦ የተራቡትን ማጉረስ እና የዜጎችን ክብር መጠበቅ እንደቻለ በተጨባጭ አሳይቷል።
የመንግሥት የልማት አቅጣጫ መዋቅራዊ መሰረተ ልማቶችን እና የሰው ተኮር ልማትን አጣጥሞ መምራት ነው።
በአንድ በኩል ታላላቅ የኃይል ማመንጫዎች እና የኢንዱስትሪ ፓርኮች ሲገነቡ፣ በሌላ በኩል ደግሞ “ከቃል እስከ ባህል” በሚል መሪ ቃል የአረጋውያንን ቤት ማደስ እና ደካሞችን መደገፍ የዕለት ተዕለት ሀገራዊ ባህል ሆኗል።
ይህ አቀራረብ እያንዳንዱ ዜጋ ከኢትዮጵያ ዕድገት እኩል ተጠቃሚ የሚሆንበትን ማኅበራዊ ፍትሕን እያረጋገጠ ነው።
ይህ እሳቤ በጥቂቶች ዘንድ ብቻ ተወስኖ እንዳይቀር በመደመር መተግበሪያ (Medemer App) በኩል በድምጽ ተቀርጾ ለሁሉም ክፍት ሆኗል።
ቴክኖሎጂን በመጠቀም እያንዳንዱ ዜጋ የሀገሩን የልማት ፍልስፍና እንዲረዳ እና የጋራ ባለቤትነት ስሜት እንዲያዳብር ተደርጓል።
በኢትዮጵያ እውን እየሆነ ያለው የልማት ስኬት የሚለካው በምናቆማቸው ሕንፃዎች ብቻ ሳይሆን በምናብሰው የዜጎች እንባ እና ለህፃናት በምናዘጋጀው አስተማማኝ ነገ ጭምር ነው።
የመደመር እሳቤ መዋቅራዊ ልማትን ከሰብዓዊነት ጋር አዋሕዶ በመጓዝ የኢትዮጵያን ዘላቂ ብልፅግና እና የዜጎችን ክብር ለማረጋገጥ የሚያስችል ዋነኛ የልማት አቅጣጫ ሆኖ ቀጥሏል።
በለሚ ታደሰ
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: