የፖለቲካ ልዩነቶችን በኃይል የመፍታት የረዥም ጊዜ ታሪካዊ ልማድን በመተው ችግሮችን በጠረጴዛ ዙሪያ በውይይት ለመፍታት የተደረገው ሀገራዊ ውሳኔ በራሱ የላቀ ስልታዊ እና ታሪካዊ ስኬት ነው።
ያለፉት ጊዜያት የግጭት አዙሪቶች እንዲሁም የዜሮ ድምር ፖለቲካ ሀገራችንን ለከፍተኛ ሰብአዊ እና ኢኮኖሚያዊ ቀውሶች ሲዳርጓት መቆየታቸው የአደባባይ ሐቅ ነው።
ይሁን እንጂ መላው ኢትዮጵያውያንን ባሳተፈው ሀገራዊ የምክክር ሒደት እነዚህን ሥር የሰደዱ መዋቅራዊ ችግሮች በዘላቂነት ለመፍታት እና መሠረታዊ በሆኑ ጉዳዮች ላይ የጋራ መግባባት ላይ ለመድረስ አዲስ የታሪክ ምዕራፍ ከፍቷል።
ይህ አካታች እርምጃ ዜጎችም ሆኑ የፖለቲካ ኃይሎች ከስሜታዊነት በጸዳ መልኩ አመክንዮን እና መረጃን መሠረት ያደረገ ገንቢ ውይይት እንዲያካሂዱ ልዩ ዕድል ፈጥሯል።
ከዚህ ቀደም ይደረጉ የነበሩ ድርድሮች በአብዛኛው በዝግ በሮች ጀርባ የሚከናወኑ እና የጥቂት ልሂቃን የጥቅም ክፍፍል ላይ ያተኮሩ ነበሩ።
በተቃራኒው የአሁኑ ሀገራዊ የምክክር ሒደት ሰፊውን ሕዝብ የድርጊቱ ቀጥተኛ ባለቤት በማድረግ በፖለቲካው መስክ ጉልህ ስብራት አምጥቷል።
ሀገራዊ ምክክሩ እስካሁን በተጓዘበት መንገድ በርካታ ታሪካዊ ክንውኖችን ማሳካት ችሏል።
ይህ ኩነት የ130 ሚሊዮን ሕዝብን ድምጽ፣ ቅሬታ እና ተስፋ ያንጸባረቀ አካታች መድረክ መፈጠሩን ያረጋገጠ ነው። መድረኩ ዜጎች ከመቼውም ጊዜ በላይ እንዲቀራረቡ፣ የሐሳብ ልውውጥ እንዲያደርጉ እና መተማመን እንዲገነቡ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አበርክቷል።
ከቀበሌ እና ወረዳ አንስቶ እስከ ፌደራል ደረጃ ድረስ የተወከሉ ተሳታፊዎች ባቀረቧቸው ስምንት ዋና ዋና የውይይት አጀንዳዎች እንዲሁም ከእነዚሁ በፈለቁ በመቶዎች የሚቆጠሩ ምክረ ሐሳቦች ላይ ሰፊ እና ጥልቅ ውይይት ተካሂዷል።
በእነዚህ አንገብጋቢ አጀንዳዎች ዙሪያ ሐሳቦች በነጻነት ተንሸራሽረው ሀገርን እና ሕዝብን አሸናፊ በሚያደርጉ ጉዳዮች ላይ የጋራ መግባባት መፈጠሩ የምክክሩን ፍሬያማነት በተጨባጭ የሚያሳይ ነው።
መድረኩ የነበረውን ጥልቀት የሚያሳየው ሌላው ጉዳይ ተመካካሪዎቹ ያነሷቸው አንኳር ሐሳቦች ናቸው።
ተሳታፊዎቹ ጦርነት እና የኃይል አማራጭ ፍጹም መፍትሔ ሊሆኑ እንደማይችሉ በማስመር፤ ዘላቂ ሰላም ማምጣት የሚቻለው በመወያየት እንዲሁም በመመካከር ብቻ መሆኑን በአጽንኦት አረጋግጠዋል።
ሰላም የሁለንተናዊ ዕድገት መሠረት በመሆኑ ሀገራዊ የምክክር መድረኩ የቆዩ የፖለቲካ ቋጠሮዎችን ለመፍታት ሁነኛ መንገድ መሆኑን በጋራ አንስተዋል።
ዲያስፖራውን ወክለው በምክክሩ የተሳተፉ ወገኖች በበኩላቸው፤ አሁን ላይ እየተከናወነ ያለው ሒደት ከውይይት ውጭ ያሉ አማራጮች አውዳሚ መሆናቸውን በሚገባ ያሳየ እና ለሌሎች ሀገራትም በአርአያነት ሊጠቀስ የሚችል አዎንታዊ እርምጃ መሆኑን መስክረዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ይህንን ታሪካዊ ምክክር አስመልክተው ባስተላለፉት መልእክት፣ መላው ኢትዮጵያውያን የዓድዋን የድል መንፈስ በመሰነቅ ለሀገር ግንባታ ያዳበሩትን ጽናት ወደ ምክክር እና መግባባት እንዲቀይሩት ዐደራ ማለታቸው የሒደቱን ሀገራዊ ፋይዳ በእጅጉ ከፍ ያደርገዋል።
ይሁን እንጂ ይህ ታሪካዊ ስኬት በቀላሉ የተገኘ አይደለም። ሀገራችን በጠንካራ መሠረት ላይ እንዳትቆም የሚፈልጉ የተለያዩ የውጭ ኃይሎች ጫና ለማሳደር ሞክረዋል።
በተጨማሪም በዲጂታል ሚዲያዎች የሐሰት መረጃዎችን በማሠራጨት ሕዝቡ ዘንድ ውዥንብር ለመፍጠር ከፍተኛ ጥረት ሲያደርጉ ቆይተዋል።
ነገር ግን ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽኑ ተቋማዊ ገለልተኝነቱን በጥብቅ በማስከበር እንዲሁም ከ54 በላይ የሚዲያ ተቋማት እና 461 ጋዜጠኞች ሒደቱን በቀጥታ እንዲዘግቡ በማድረግ የተዛቡ መረጃዎችን በከፍተኛ ግልጽነት ማከሸፍ ችሏል። ውይይቶቹ ከስሜታዊነት ይልቅ በጥናት፣ በማስረጃ እና በምክንያታዊነት ላይ እንዲመሠረቱ በመደረጉ በጥላቻ ላይ የተገነቡ ትርክቶች ቦታ እንዳያገኙ አድርጓል።
በአጠቃላይ ይህ ስኬታማ ታሪካዊ ክንውን ሀገራችን የውጭ ጫናዎችን፣ የሐሰት ትርክቶችን እና የተደራጁ ውዥንብሮችን በጽናት በመቋቋም የራሷን ዕጣ ፈንታ በገዛ እጇ መወሰን እንደምትችል በተግባር ያረጋገጠ ነው።
ሕዝቦቿ በጋራ አሸናፊ የሚሆኑበትን ዘላቂ የሰላም እና የብልጽግና ፍኖት በአስተማማኝ ሁኔታ እውን እያደረገች መሆኗንም በሚገባ ያሳየ ታላቅ ድል ነው።
በለሚ ታደሰ
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: